ቅድመ ዳሰሳ | ሰበታ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በመጨረሻ ጨዋታዎቻቸው ሀዋሳ ከተማን ያሸነፉት ቡድኖች እርስ በእርስ የሚያደርጉትን ጨዋታ እንዲህ ዳሰነዋል።

የሁለተኛው ሳምንት አራፊ የነበረው ሰበታ ከተማ በከባዱ መርሐ ግብር ወደ ጨዋታ ይመለሳል። ሁለተኛው ሳምንት ላይ ሀዋሳ ከተማን እምብዛም ሳይቸገር በመርታት የመጀመሪያ ድሉን ያስመዘገበው ሰበታ እንዳለፉት ጨዋታዎች ሁሉ በአንጋፋ አማካዮቹ መሪነት ነገም ለኳስ ቁጥጥር ዝንባሌ ያለው አቀራረብን ይዞ እንደሚገባ ይጠበቃል። በዚህም አካሄድ መሀል ሜዳ ላይ የተጋጣሚው ተጫዋቾችን ፍጥነት የመቆጣጠር እና ያልተሳኩ ቅብብሎችን ቁጥር መቀነስ በእጅጉ ያስፈልገዋል። በተለየም ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ የሚታይበት መዳከም ለተደጋጋሚ መልሶ ማጥቃቶች በር እንዳይከፍት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል። በሀዋሳው ጨዋታ በተከላካይ አማካይ ቦታ ላይ የተሰለፈው ቢያድግልኝ ኤልያስ የሮቢን ንግላንዴን የማጥቃት ተሳትፎ ከመቆጣጠር ባለፈ ቡድኑ መሀል ሜዳ ላይ ኳስ የሚያጣባቸው ቅፅበቶች ወደ ሳጥኑ እንዳይደሩሱ የማድረጉን ሂደት እንደሚመራ ይጠበቃል። በማጥቃቱ ረገድ መልካም አቋም ላይ የሚገኘው ፉዐድ ፈረጃ ከቀኝ ወደ መሀል እያጠበበ የሚገባባቸው ፣ ቡልቻ ሹራ ከፊት አጥቂነቱ መለስ በማለት ከአማካይ መስመሩ ጋር የሚገናኝባቸው እንዲሁም ከአጥቂ አማካዮቹ የሚሰነጠቁ ድንገተኛ ኳሶች የሚኖሩባቸው ቅፅበቶች ተጠባቂ ይሆናሉ።

በተመሳሳይ ሁኔታ በሰፊ የግብ ልዩነት ሀዋሳን አሸንፈው ወደዚህ ጨዋታ የሚመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ለሦስተኛ ተከታታይ ድል ይፋለማሉ። ቡድኑ ነገም ኳስን ይዞ ለመጫወት መሞከሩ የሚጠበቅ ቢሆንም ቀጥተኛ ኳሶቹ እና የሜዳውን ስፋት በመጠቀም የተጋጣሚውን የኋላ ክፍል ተሰላፊዎች መሀል ክፍተት ለመፍጠር የሚሞክርበት ሂደትም ተጠባቂ ነው። በግል ደረጃ የጌታነህ ከበደ በሙሉ አቅም ወደ ሜዳ መመለስ እና ግቦችንም ማስቆጠር ለፈረሰኞቹ በራስ መተማመን የጨመረ ይመስላል። የአቤል ያለው ከአዲስ ግደይ ጋር ቦታ በመቀያየር ከመስመሮች በመነሳት ወደ ውስጥ ኳስ የሚነዳበት መንገድም ጊዮርጊስን በፈጣን ሽግግር ወቅት አስፈሪነትን ያላበሰው ሌላው ነጥብ ሆኗል። ኃይለሚካኤል አደፍርስ እና የቀድሞው ክለቡን የሚገጥመው ዓለምአየሁ ሙለታ የሰበታ የመስመር ተከላካይነት ሚናም ይህንን የተጋጣሚ እንቅስቃሴ በመግታት ረገድ የሚፈተን ይሆናል። ከዚህ ውጪ አማካይ ክፍል ላይ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በመያዝ እና መስርቶ ለመውጣት የሚረዱ የጎንዮሽ ቅብብሎችን በመከወኑ ረገድ ጊዮርጊሶች በልምድ ላቅ ከሚለው የተጋጣሚያቸው የመሀል ክፍል ጋር ብርቱ ፍልሚያ የሚጠብቃቸው ይመስላል።

በነገ ረፋዱ ጨዋታ ሰበታ ከተማ ተቀይሮ በመግባት ጥሩ ሲንቀሳቀስ ከነበረው ዱሬሳ ሹቢሳ ጉዳት ውጪ በጉዳትም ሆነ በኮቪድ ምክንያት የሚያጣው ተጫዋች አይኖርም። በኮቪድ ሳቢያ በሀዋሳው ጨዋታ ያልነበሩ ሦስት ተጫዋቾችም ወደ ግልጋሎት እንደሚመለሱ ይጠበቃል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ ከሚገኙት ተጫዋቾች ውስጥ አስቻለው ታመነ እና ናትናኤል ዘለቀ ወደ ልምምድ ቢመለሱም ለነገ ግን እንደማይደርሱ ታውቋል። ከዚህ ውጪ ሳላዲን በርጌቾ እና ባህሩ ነጋሽ አሁንም ጉዳት ላይ ሲሆኑ የደስታ ደሙ መድረስም አጠራጣሪ ሆኗል። ሙሉዓለም መስፍን ለነገ ጨዋታ እንደሚርስም ተነግሯል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– የዓምናውቹ ውጤቶች መሰረዛቸውን ተከትሎ ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ ከስምንት ዓመታት በኋላ ይገናኛሉ። በአጠቃላይ በሊጉ ስድስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሦስቱን በማሸነፍ የበላይነት አለው። በሁለቱ አቻ ሲለያዩ በአንዱ ሰበታ አሸንፏል።

– በስድስቱ ጨዋታዎች ዘጠኝ ጎሎች ሲቆጠሩ ስድስቱን ጊዮርጊስ ሦስቱን ሰበታ አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)

ፋሲል ገብረሚካኤል

አለማየሁ ሙለታ – መሳይ ጻውሎስ – አዲስ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

ቢያድግልኝ ኤልያስ – መስዑድ መሀመድ

ፉዓድ ፈረጃ – ዳዊት እስጢፋኖስ – ታደለ መንገሻ

ቡልቻ ሹራ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ፓትሪክ ማታሲ

አብዱልከሪም መሀመድ – ምንተስኖት አዳነ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሄኖክ አዱኛ

ሀይደር ሸረፋ – ሙሉዓለም መስፍን

አቤል ያለው – ሮቢን ንግላንዴ – አዲስ ግደይ

ጌታነህ ከበደ


© ሶከር ኢትዮጵያ