የአልጄርያ እና ኢትዮጵያ ጨዋታ የተመልካች እጦት ስጋት ተደቅኖበታል

የአልጄሪያ እግርኳስ ማህበር ለጨዋታው ከመደበው 23800 ትኬት ውስጥ እስካሁን 7000 ትኬቶች ብቻ መሸጣቸውን የአልጄርያ ፕሬስ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡ በቲኤስኤ ዘገባ መሰረት ደግሞ ጨዋታው ደረግ 24 ሰአት እስኪቀረው ድረስ የተሸጠው ትኬት 4000 ብቻ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች ብሊዳ ላይ ሲደረጉ በርካታ ተመልካች ስታድየም ቢገኝም በዛሬ ምሽቱ ጨዋታ አልጄርያውያን ከዋክብቶቻቸውን የመመልከት ፍላጎታቸው ቀዝቅዟል፡፡

የስታድየሙ ማናጀር ሙስጣፋ ዛይዶኒ ለኤፒኤስ እንደተናገረው የትኬት ሽያጩ እሁድ ቢጀመርም በሃገሪቱ ባለው ቀዝቃዛ የአየር ንብረት ምክንያት አልጄርያውያን ከቤታቸው ወጥተው ጨዋታውን የመከታተል ፍላጎታቸው ተቀዛቅዟል፡፡

የስታድየሙ ማናጀር ይህን ቢሉም ብሄራዊ ቡድኑ ከቫሂድ ሃሊልዞቪች መልቀቅ በኋላ በሚያሳየው አቋም ደጋፊዎች ደስተኛ እንዳልሆኑ ቲኤስኤ የተባለ የዜና አውታር ዘግቧል፡፡ ቲኤስኤ በተጨማሪም አልጄርያውያን ለጨዋታው የሰጡት ግምት አናሳ መሆኑ ለተመልካች ቁጥር መቀነስ እንደምክንያት አስቀምጧል፡፡

የስታድየሙ ማናጀር ዛይዶኒ ምንም እንኳን የእስካሁኑ ፍላጎት አጥጋቢ ባይሆንም በመጪዎቹ ሰአታት የተመልካቹ ቁጥር እንደሚጨምር ተስፋ አድርገዋል፡፡ ከሌሎች የሃገሪቱ ግዛቶች የሚመጡ ደጋፊዎች በአየር ንብረቱ ምክንያት በመዘግየታቸውም ብሊዳ ሲደርሱ የተመልካቹ ቁጥር ይጨምራል ብለዋል፡፡

37000 ተመልካች የማስተናገድ አቅም ያለው የብሊዳ ሙስጣፋ ቻክር ስታድየም ጥላ የሌለው መቀመጫ 300 የአልጄርያ ዲናር (2.73 ዩኤስ ዶላር) ሲያስከፍል ጥላ ያላቸው መቀመጫዎች እስከ 1300 የአልጄርያ ዲናር (11.83 ዩኤስ ዶላር) ያስከፍላሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *