‹‹ስብስባችን የነገውን ጨዋታ ለማሸነፍ ያለው ተነሳሽነት ከፍተኛ ነው›› ሎዛ አበራ

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከአልጄርያ ጋር የሚያደርገው የመልስ ጨዋታው ነገ በአዲስ አበባ ስታድየም 10፡00 ላይ ይካሄዳል፡፡ ኢትዮጵያ በአልጀርስ የደረሰባትን ሽንፈት ለመቀልበስ ከምትተማመንባቸው አጥቂዎች ግንባር ቀደሟ የሆነችው ሎዛ አበራ የነገውን ጨዋታ ለማሸነፍ እንደተዘጋጁ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገችው ቆይታ ተናግራለች፡፡

‹‹ የአልጀርሱ ጨዋታ ጥሩ ነበር፡፡ በታክቲኩም ረገድ ጥሩ ነበርን፡፡ ጨዋታውን ተቆጣጥረን ተጫውተነ ውጤት ይዘን ለመውጣት ያደረግነው ጥረት መልካም ነበር፡፡ አልጄርያዎች በራሳችን ስህተት ግብ አስቆጥረው ቢያሸንፉንም በእንቅስቃሴ ረገድ ሁለታችንም ጥሩ ተንቀሳቅሰናል፡፡ ›› የምትለው ሎዛ ከአልጀርስ መልስ የጨዋታውን ውጤት ለመቀልበስ እየተዘጋጁ እንደሆነ ትናገራለች፡፡

‹‹ ከአልጀርስ ከተመለስን በኋላ በድክመቶቻችን ላይ ተነጋግረን ነው ልምምድ የጀመርነው፡፡ በመልሱ ጨዋታ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ለማድረግ ስለምናስብ ያንን ለመተግበር ጥሩ ተዘጋጅተናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከግብ ጠባቂ ጀምሮ እስከ አጥቂዎች ድረስ ሙሉ ስብስቡ ጨዋታውን አሸንፎ ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ ያለው ተነሳሽነት ከፍተኛ ነው፡፡ በተጫዋቾች መካከል ያለው የእርስ በእርስ ግንኙነት መግባባት ጥሩ ስለሆነ አሸንፈን እናልፋለን፡፡ ››

በአለም ከ20 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ 6 ግቦች በማስቆጠር ኢትዮጵያን ከጫፍ አድርሳ የነበረችው ሎዛ በነገው ጨዋታም ግቦች እንድታስቆጥር ሃላፊነት ተጥሎባታል፡፡ ብዙዎች ከሎዛ ግቦች ቢጠብቅም የደደቢቷ አጥቂ ጨዋታውን ለማሸነፍ እንደቡድን መጫወት እንደሚገባ ትገልጻለች፡፡

‹‹ ግብ የማስቆጠር ሃላፊነት የእኔ ብቻ አይደለም፡፡ በጋራ እንደቡድን መንቀሳቀስ ስንችል ነው ልናሸንፍ የምንችለው፡፡ ነገር ግን እኔ በግሌ መክፈል የሚገባኝን መስዋዕት ሁሉ ከፍዬ ሃገሬን አንድ ደረጃ ከፍ ለማድረግ በጣም ዝግጁ ነኝ፡፡ ከልጅነቴ ላሳከው ስፈልገው የኖርኩት የብሄራዊ ቡድን ማልያ የመልበስ ምኞቴን አሳክቻለሁ፡፡ ያገኘሁትን እድል ሃገሬን ትልቅ ደረጃ በማድረስ ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡›› ብላለች፡፡

PicsArt_1458898992877

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *