“የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ፍጥነት ሊያስቸግረን ይችላል” – ዋሊድ መስሉብ

ለፈረንሳዩ ሎርዮ ክለብ የሚሰለፈው አልጄሪያዊ ዋሊድ መስሉብ የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ለተጋጣሚው ዝቅተኛ ግምት ሰጥቶ መግባት እንደሌለበት ተናግሯል። ዋሊያዎቹ ፈጣን እና ጥሩ የእግርኳስ ክህሎት ያላቸው በመሆኑ አልጄሪያውያኑ ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ መከተል እንዳለባቸው ነው ተጫዋቹ የገለፀው።

“ከኢትዮጵያ ጋር የምናደርጋቸው ሁለቱ ጨዋታዎች ለእኛ እጅግ አስፈላጊ እና ለአፍሪካ ዋንጫው የማለፍ ዕድላችንን የሚወስኑ መሆናቸው ግልፅ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፈጣን እና ጥሩ የቴክኒክ ችሎታ ያላቸው ተጫዋቾች የሚገኙበት ቡድን ነው። ስለዚህ ለተጋጣሚያችን ተገቢውን ክብር ሰጥተን በጥንቃቄ መጫወት ይኖርብናል፤” ሲል ያለውን አስተያየት ሰጥቷል።

የ30 ዓመቱ የአማካይ ሀገሩ ለመጨረሻ ጊዜ ባደረገችው ጨዋታ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ታንዛኒያን 7-0 ያሸነፈች መሆኑ ወደዛሬው ጨዋታ በልበ ሙሉነት እንዲገቡ ያስቻላቸው መሆኑን የተናገረ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከብሊዳው ጨዋታ ይልቅ አዲስ አበባ ላይ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ያለውን ግምት ሰንዝሯል።

“ምድቡን እየመራን መሆናችን እና የመጀመሪያውን ጨዋታ በሃገራችን መጫወታችን የአዲስ አበባውን የመልስ ጨዋታ የሚያቀልልን ይሆናል። ነገር ግን ከ2000 ሜትር በላይ በሆነ ከፍታ ላይ ባለችው አዲስ አበባ የሚኖረን ጨዋታ ፈታኝ መሆኑ አይቀርም። በፍጥነት አየር ንብረቱን በመላመድ ሁለቱንም ጨዋታዎች ለማሸነፍ መስራት ይኖርብናል። ለጊዜው ግን ሙሉ ትኩረታችን በብሊዳ በሚደረገው ጨዋታ ላይ ነው።”

የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን የኢትዮጵያ አቻውን ዛሬ ከምሽቱ 4፡30 ላይ ቢልዳ በሚገኘው ሙስታፋ ቻከር ስታዲየም የሚያስተናግድ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *