ክርስቲያን ጎርኩፍ ከኢትዮጵያ የደርሶ መልስ ጨዋታ በኋላ ሰራቸውን ሊለቁ ይችላሉ

የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድንን ዋና አሠልጣኝነት ወንበር በሐምሌ ወር 2006 ዓ.ም. ከቫሂድ ሃሊልሆድዚች የተረከቡት ፈረንሳዊ አሠልጣኝ ክርስቲያን ጎርኩፍ ቡድናቸው ከኢትዮጵያ ጋር ከሚያደርገው የደርሶ መልስ ጨዋታ በኋላ ከሃላፊነታቸው እንደሚለቁ በስፋት እየተነገረ ይገኛል።

አሠልጣኙ ባለፈው ህዳር ወር ላይ ከአልጄሪያ ሚዲያ እና በአንዳንድ ጨዋታዎች ላይ ቡድኑ ባሳየው እንቅስቃሴ ደስተኛ ካልነበሩ ደጋፊዎች ጋር በተፈጠረ ግጭት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ሊለያዩ ቀርበው የነበረ ቢሆንም ተጫዋቾቹ እና የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ በሰጧቸው ድጋፍ ምክኒያት ለመቆየት ወስነዋል። አሁን ከአልጄሪያ እንደሚወጡ ዘገባዎች ከሆነ ግን አሠልጣኝ ጎርኩፍ ከእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንት መሃመድ ራውራዋ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገብተዋል።

መሃመድ ራውራዋ አሠልጣኙ ከስራቸው እንዲሰናበቱ ፍላጎት እንዳላቸው የተሰማ ሲሆን በቅርቡ የቀድሞውን የሪያል ማድሪድ አሠልጣኝ ራፋኤል ቤኒቴዝ ወደ አልጄሪያ ለማምጣት ጥረት ሲያደርጉ ነበር። በተፈጠረው ውጥረት ምክኒያትም አሠልጣኝ ጎርኩፍ ቀድሞ የሚኖሩበት አልጄሪያን ለቀው አመዛኙ ጊዜያቸውን በፈረንሳይ በማሳለፍ እና ጨዋታ በሚኖርበት ጊዜ ብቻ ወደ አልጄሪያ በመመለስ እየሰሩ ይገኛሉ።

ጎርኩፍ ከ3 የፈረንሳይ ክለቦች ጋር ከወዲሁ ድርድር እንደጀመሩ የወጡ መረጃዎች ሲያመለክቱ ወደ ናንቴስ ክለብ የማምራት ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነ ተነግሯል። አሠልጣኙ የወደፊት ቆይታቸውን ከመወሰናቸው በፊት ግን የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድንን እየመሩ ከኢትዮጵያ ጋር በብሊዳ እና አዲስ አበባ ሁለት ጨዋታዎች የሚያደርጉ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *