የአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን ትላንት ምሽት አዲስ አበባ በመግባት በሸራተን ሆቴል መቀመጫቸውን አድርገዋል፡፡ በዛሬው እለትም ጨዋታው በሚደረግበት አዲስ አበባ ስታድየም ልምምዳቸውን አከናውነዋል፡፡
አሰልጣኝ ክርስቲያን ጉርኩፍ ለማጣርያው የመረጧቸው 24 ተጫዋቾች በሙሉ አዲስ አበባ ይዘው የመጡ ሲሆን በዛሬው እለትም ሁሉም ተጫዋቾች ልምምድ ሰርተዋል፡፡ በልምምዳቸውም ለሁለት ተከፍለው ጨዋታ ያደረጉ ሲሆን ከኳስ ጋር የመዝናናት እና የማላቀቅ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡
በልምምድ ፕሮግራሙ መጨረሻ በስፍራው የተገኙ ስፖርት አፍቃርያን ከቡድኑ ከዋክብት በተለይም ከሪያድ ማህሬዝ ጋር ፎቶ ለመነሳት ጥረት ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ እና አልጄርያ ጨዋታ ነገ 11፡00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ሲደረግ አልጄርያ ድል ቀንቷት ሲሸልስ ደግሞ ሌሶቶ ላይ ነጥብ ከጣለች ለ2017 የጋቦን የአፍሪካ ዋንጫ አስቀድማ ማለፏን ታረጋግጣለች፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ካሸነፈች ከአልጄርያ ጋር ያላትን የነጥብ ልዩነት ወደ 2 ታጠባለች፡፡
ጨዋታውን ከሰሃራ በታች ላሉ ሃገራት በቀጥታ የሚያስተላልፈው ሱፐር ስፖርት ጊዜያዊ ስቱድዮውን በመያዝ ከኬንያ ተነስቶ ቅዳሜ አዲስ አበባ ገብቷል፡፡