‹‹ ወደ ጋቦኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችንን የሚያረጋግጥልንን ውጤት ይዘን መመለስ እንፈልጋለን››  የአልጄርያው አሰልጣኝ ክሪስቲያን ጉርኩፍ

የአልጄርያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ክሪስቲያን ጉርኩፍ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያው 3ኛ ጨዋታ አልጄርያ በኢትዮጵያ ላይ የ7-1 ድል ከመሩ በኋላ ለ ፌኔክስን ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማሳለፍ ተቃርበዋል፡፡ 

ፈረንሳያዊው አሰልጣኝ በአርቡ ድል እና በነገው ጨዋታ ዙርያ ለጋዜጠኞች የሰጡትን መግለጫ ከተለያዩ የአልጄርያ ሚድያዎች በማጣቀስ እንዲህ አቅርበነዋል፡- 

‹‹ግብ ማስተናገድ አልነበረብንም››

‹‹ ሁሉም ነገር ባቀድነው መሰረት ተግባራዊ አድርገናል፡፡ በፈጣን እንቅስቃሴ ተጋጣሚያችን በራሱ የግብ ክልል ተገድቦ እንዲጫወት ማድረግና ጨዋታውን ራሳችን በምንፈልገው ፍጥነት እንዲሄድ ነበር አላማችን፡፡ የጨዋታው መጀመርያ አካባቢ እንስቃሴያችን ዝግ ያለ ቢሆንም የኋላ ኋላ ተጋጣሚያችንን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከተናቸዋል፡፡

‹‹ ከዚህም በላይ ልዩነት የመፍጠር ትኩረት እና ትዕግስት የታደሉ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾ ይዘናል፡፡ እደመከነው የፍፁም ቅጣት ምት እና ያልተጠቀምንባቸው በርካታ የግብ እድሎች ባይሆን ውጤቱ ከዚህም በላይ ይሰፋ ነበር፡፡ ነገር ግን ጨዋታው ልዩ ነበር፡፡ ትልቅ ግብም አሳክተናል፡፡ ፍፁም የሆነ ምሽት አሳልፈናል፡፡

‹‹ በጨዋታው ላይ ቅር የሚለኝ ነገር ቢኖር የተቆጠረብን ግብ ነው፡፡ ግብ ሳናስተናግድ ለመውጣት ተመኝቼ ነበር፡፡ ቡድኔ በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ባሳየው እንቅስቃሴ ደስተኛ አይደለሁም፡፡ ሁልጊዜም በትኩረት እና ንቃት ለ90 ደቂቃ መንቀሳቀስ አለብን፡፡ ቡድኔ በተሰጥኦ የተሞላ ነው፡፡ ነገር ግን ጨዋታዎችን በብስለት ማሸነፍም ይኖርብናል፡፡ ”

የመልሱ ጨዋታ

‹‹ ከአየሩ አስቸጋሪነት በተጨማሪ የሜዳው ደረጃ ለመጫወት አስቸጋሪ ያደርግብናል፡፡ ነገር ግን በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ወቅትም በዚሁ ሜዳ ላይ ጨዋታ አድርገናል፡፡ ያን ጊዜ በጣም ተቸግረን ነበር፡፡ አሁንም ከዛ የተለየ ነገር አይኖርም፡፡

‹‹ በጨዋታው እንቅስቃሴያችንን ከሜዳው ጻባይ ጋር ማላመድ ይጠበቅብናል፡፡ ነገር ግን ውጤታማነታችን የነገውን ጨዋታ ከፍ ባለ ተነሳሽነት እንድንጫወት ያግዘናል፡፡ ለተጋጣሚያችን ያለን አክብሮት እንዳለ ሆኖ መልካም ውጤት ይዘን ለመመለስ ነው የመጣነው፡፡

‹‹ ጨዋታውን ለማሸነፍ ነው የመጣነው፡፡ 3 ነጥብ ይዘን ወደ ሃገራችን ለመመለስ የሚያስችል አቅም አለን፡፡ የአርቡ ጨዋታ ውጤት በተጋጣሚዎቻችን ላይ የስነልቦና በላይነት እንድናገኝ ረድቶናል፡፡ ወደ ጋቦኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችንን የሚያረጋግጥልንን ውጤት ይዘን መመለስ እንፈልጋለን፡፡ ”

ከተጫዋቾቻቸው ጋር ስላላቸው ግንኙነት  

” አንዳንድ ሚድያዎች ተፃራሪ ዘገባዎችን ቢያወጡም ከተጫዋቾቼ ጋር መልካም ግንኙነት አለኝ፡፡ የብሄራዊ ቡን አሰልጣኝ እንደመሆኔ ተጫዋቾቹን የማገኝበት ጊዜ እጅግ ውስን ነው፡፡ ሆኖም ሁልጊዜም ከተጫዋቾቼ ጋር መልካም ግንኙነት አለኝ፡፡ በስብስባችን ውስጥ ምርጥ የቡድን መንፈስ አለ፡፡ ”

ምንጮች – ዲዚ ፉት ፣ ሞጃሂድ ፣ ሊበርቲ ፣ ኤኤንኤስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *