ለ2017 የጋቦን የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አልጄርያን አስተናግዶ በጨዋታው መገባደጃ በተቆጠረበት ግብ 3-3 አቻ ተለያይቷል፡፡
በብሊዳ በተደረገው ጨዋታ 7-1 የተሸነፈው ብሄራዊ ቡድናችን በደጋፊዎች ዘንድ መቀዛቀዝን ያስከተለ የተመልካች ድርቅ ይኖራል ተብሎ ቢጠበቅም በተቃራኒው ስታድየሙ እንደተለመደው በተመልካች ተሞልቶ ጨዋታው ተካሂዷል፡፡ ዋልያዎቹም ከአርቡ ሽንፈት ፍጹም በተለየ መልኩ መልካም እንቅስቃሴ በማድረግ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል፡፡
ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዘችው ኢትዮጵያ ስትሆን በ29ኛው ደቂቃ ታደለ መንገሻ ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ራሱን ነፃ አድርጎ የቆመው ጌታነህ ከበደ በማስቆጠር ዋልያዎቹን መሪ አድርጓል፡፡ በመጀመርያው አጋማሽ ደካማ እንቅስቃሴ ያሳዩት እልጄርያዎች የሪያድ ማህሬዝ እና ዋሊድ መስሎብ ክህሎትን ተጠቅመው የመጀመርያውን አጋማሽ በአቻ ውጤት ጨርሰዋል፡፡ በ43ኛው ደቂቃ ማህሬዝ በጥሩ ሁኔታ ያሾለከለትን ኳስ ዋሊድ መስሎብ ተቆጣጥሮ በግሩም ሁኔታ ለስሊማኒ ያሻገረውን ኳስ የስፖርቲንጉ አጥቂ ኢስላም ስሊማኒ ተወርውሮ በግንባሩ በመግጨት ከመረብ አሳርፏል፡፡
የሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ብዙም ሳይቆይ በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው ታደለ መንገሻ ያሻገረውን ኳስ ጌታነህ በግሩም አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ ኢትዮጵያን በድጋሚ መሪ አድርጓል፡፡ ከግቧ በኋላ ጫና የፈጠሩት ዋልያዎቹ በጌታነህ ከበደ ፣ ሽመልስ እና ተቀይሮ በገባው ዳዊት ፍቃዱ አማካኝነት የግብ እድል ቢፈጥሩም ሬይስ ምቦሊ አድኖባቸዋል፡፡ በ61ኛው ደቂቃ በኢትዮጵያ ተከላካዮች የትኩረት ማነስ ያገኙትን የማዕዘን ምት ተከላካዩ አይሳ ሜንዲ በግንባሩ በመግጨት አልጄርያን በድጋሚ አቻ አደርጓል፡፡
አልጄርያዎች የአቻነት ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በ64ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ አክርሮ የመታውን ኳስ ሬይስ ሲመልሰው በቅርብ ርቀት የነበረው ዳዊት ፍቃዱ አግኝቶት ኢትዮጵያን ለሶስተኛ ጊዜ መሪ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል፡፡
በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ጨዋታው የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን በሁለቱም በኩል ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡ በ84ኛው ደቂቃ ተከላካዩ አንተነህ ተስፋዬ በኢትዮጵያ የግብ ክልል ውስጥ ያቺን ብራሂሚን በመጥለፉ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት የግራ መስር ተከላካዩ ፋውዚ ጉልሃም ወደ ግብነት ቀይሮ አልጄርያን አቻ አድርጓል፡፡ ጨዋታውም 3-3 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ አልጄርያ በ10 ነጥብ ምድቡን መምራቷን ስትቀጥል ኢትዮጵያ 5 ነጥብ በመያዝ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ሲሸልስ በ4 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ ሌሶቶ በ3 ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች፡፡