ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከ መቻል ጋር ያገናኘው ጨዋታ ያለ ግብ 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ በምሽቱ መርሐግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከመቻል ያገናኘው ተጠባቂ ጨዋታ ነበር። ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በባለ ሜዳው ሀዋሳ ከተማ የ 2-1 ሽንፈት ካስተናገዱበት ጨዋታ ይዘውት ከገቡት ቋሚ አሰላለፍ ተመስገን ተስፋዬ ፣ ቢንያም ካሳሁን እና ዳዊት ዮሐንስን በማሳረፍ በምትካቸው ካሌብ አማንክዋህ ፣ዘላለም አበበ እና በዛብህ ካቲሴን ሲያስገቡ በተመሳሳይ መቻሎች አዳማ ከተማዎች ላይ ድል ከተቀዳጁበት አሰላለፍ ግሩም ሀጎስን በአስቻለው ታመነ ብቻ በመቀየር ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
የዛሬው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ማሸነፍ ሚችሉ ከሆነ ደረጃቸውን በማሻሻል ወደ መሪዎቹ የሚጠጉበትን ዕድል የሚፈጥር መሆኑ ተጠባቂ አድርጓታል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ካደረጉት የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፈው በሁለቱ ተሸንፈው በአንዱ ደግሞ ነጥብ የተጋሩ ሲሆን መቻል ደግሞ አራቱን አሸንፈው በአንዱ ብቻ ተሸንፈው የዛሬ ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
ጨዋታው ከጅማሬው አንስቶ ጥሩ የሆነ የኳስ እንቅስቃሴን ያስመለከተን አጋማሽ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ግቦችን ለማስቆጠር ፈጣን በሆነ ሽግግር ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ሲሆን 9ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከግብጠባቂው ፍሬው ጌታሁን የተመታውን ኳስ የመቻሉ ግብ ጠባቂ ለመያዝ ሲሞክር ያለፈውን ኳስ ተሯሩጦ ያገኘው ናትናኤል ዳንኤል የመታው ኳስ በግቡ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል ይሄም አስቆጪ የሚባል የግብ አጋጣሚ ነበር።
ጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴ ያሳየን ሲሆን ተራ በተራ ብልጫ በመውሰድ ለማጥቃት ሙከራ ሲያደርጉ ተስተውሏል የመጀመሪያዎቹን 15 ደቂቃዎች መቻሎች በማጥቃቱ ረገድ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን የተቀሩትን ደቂቃዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ጥሩ የሆነ እንቅስቃሴን አስመልክተውናል። ነገር ግን ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ይሄ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሳያስመለክተን የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ቀዝቀዝ ያለ ጨዋታን ያስመለከተን ሲሆን በማጥቃቱ ረገድ ሁለቱም ቡድኖች ተዳክመው ቀርበዋል። ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ሙከራ ሳያስመለክቱን ቢቆዩም 70ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ የንግድ ባንክ ተጫዋቾችን ኳስ በማቋረጥ ወደ ሳጥኑ ጠርዝ በመጠጋት የመታው ኳስ አስቆጪ በሆነ መንገድ ለጥቂት በግቡ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል። ጨዋታውም በዚህ ቀጥሎ በአጋማሹ ምንም አይነት ይሄ ነው የሚባል የግብ ሙከራን ሳያስመለክተን 0-0 በሆነ ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል።