አዞዎቹ እና የሊጉ መሪ መድን የሚያገናኘውን ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በተከታታይ ድሎች ሁለተኛውን ዙር ቢጀምሩም ቀጥለው በተካሄዱ ጨዋታዎች መጠነኛ መደነቃቀፍ የገጠማቸው አዞዎቹ ከሊጉ መሪ ጋር በሚያደርጉት የነገው ጨዋታ ድል ማድረግ ከ4ኛ እስከ 5ኛ ደረጃ ላይ ተከታትለው ከተቀመጡት ቡድኖች በነጥብ እንዲስተካከሉ ይረዳቸዋል።
አዞዎቹ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በውጤትም ይሁን በእንቅስቃሴ ደረጃ የወጥነት ችግር ተስተውሎባቸዋል። በውድድር ዓመቱ የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን ሆኖ የዘለቀው የማጥቃት ጥምረቱ በተለይም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ያሳየው መጠነኛ መዳከምም ለተቀዛቀዘው ውጤት እንደ ዋነኛ ምክንያት መጥቀስ ይቻላል። ቡድኑ በ2ኛው ዙር የመጀመርያ አምስት መርሐ-ግብሮች በድምሩ ሰባት ግቦች ማስቆጠር ቢችልም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ግን ግብ ካለማስቆጠሩም በተጨማሪ በርከት ያሉ የላቁ የግብ ዕድሎችን መፍጠር አልቻለም። ጥቂት ግቦች ያስተናገደው የነገው ተጋጣሚያቸው መድን ደግሞ በቀላሉ ግቡን የሚያጋልጥ ቡድን ስለሆነ የሚገኙ አጋጣሚዎችን በስልነት መጠቀም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
አሰልጣኝ በረከት ደሙ እስካሁን በአመዛኙ ከኳስ ጋር ብልጫ ሊወስዱበት የሚችሉ ተጋጣሚዎችን በመልሶ ማጣቃት ፈትኖ ውጤት ሲያሳካ በተደጋጋሚ ቢታይም በነገው ዕለት በተመሳሳይ አኳኋን ለመጫወት የማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት ከፍ ማድረግ ይኖርበታል።
በሀምሳ አንድ ነጥቦች በሊጉ አናት ላይ የተሰየመው ኢትዮጵያ መድን በጊዜ ዋንጫውን በእጁ ለማስገባት የሚያደርገውን ጉዞ ለማሳለጥ በነገው ዕለት ድል ማድረግ እጅግ አስፈላጊው ነው።
በሁለተኛው ዙር የመጀመርያ መርሐ-ግብር በወላይታ ድቻ ከገጠመው ሽንፈት አገግሞ ወደ ውጤት ጎዳና መመለሱ እንዲሁም ተከታዮቹ ነጥብ
መጣላቸውን ተከትሎ መሪነቱን ያጠናከረው ቡድኑ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ስምንት ነጥብ አስራ ስድስቱን ማሳካቱ ለምን መሪነቱ ላይ እንደተቀመጠ ማሳያ ነው። ቡድኑ ተከታታይ ድሎች ባስመዘገበባቸው ስድስት የጨዋታ ሳምንታት አስራ አንድ ግቦች አስቆጥራል ፤ የጎለበተው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው እና እጅግ የተሻሻለው የግብ ማስቆጠር ብቃቱም በቀጣይ ጨዋታዎች በዚህ አኳኋን የሚቀጥሉ ከሆነም የሊጉን አሸናፊነት በጊዜ የሚያውጅበት ዕድል ስፊ ነው።
የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌው ቡድን በማጥቃቱ ረገድ የሚታይ መሻሻል አሳይቶ በርከት ያሉ ግቦች በማስቆጠር ላይ ቢገኝም በመጨረሻው ጨዋታ ከአራት መርሐ-ግብሮች መልስ መረቡን አስከብሮ የወጣውን የኋላ ክፍል ጥንካሬ ማስቀጠል ግድ ይላቸዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 7 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ አምስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ኢትዮጵያ መድን ሁለት ጊዜ ድል አድርጓል።