ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሀዋሳ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሀዋሳ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው የጨዋታ ሳምንቱ መገባደጃ መርሐ-ግብር ለተጋጣሚዎቹ ብቻ ሳይሆን በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ያሉ እና ለቀጠናው የቀረቡ ቡድኖችን ሁሉ ይመለከታል።

ሁለት ጣፋጭ ድሎች ማግኘታቸውን ተከትሎ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ጫፍ የደረሱት ሀዋሳ ከተማዎች በነገው ዕለት ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን ማስመዝገብ ከቻሉ ለወራት ከዳከሩበት ወራጅ ቀጠና መውጣት የሚችሉበት ዕድል እጃቸው ላይ ይገኛል።

በሀይቆቹ ቤት ነገሮች ጥሩ እየሄዱ ነው። ፈጣን የመልሶ ማጥቃት ላይ መሰረት ያደረጉት የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ትርጉም ያላቸው እየሆኑ በታዩባቸው ያለፉት ጨዋታዎች ዓሊ ሱሌይማንን ያነጣጠሩ ከአማካይ መስመር የሚነሱ ጥቃቶች ጥሩ ውጤት እያስገኙ ይገኛል። ነገም ይህን መሻሻል ከጠንካራው የሲዳማ ተከላካይ ጋር ማስቀጠል መቻል ለቡድኑ እጅግ ወሳኝ ይሆናል።
በ14ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው መቐለ 70 እንደርታ በአንድ ነጥብ እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ በሀያ ሰባት ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሀዋሳ ከተማ በነገው ዕለት ድል ማድረግ ለቡድኑ ዘርፈ ብዙ ትርጉም አለው፤ የመጨረሻ ሁለት ሳምንታት ድሉም በሥነልቦናው የተረጋጋ ቡድንን ነገ ለማሳየት እንደሚረዳው ይጠበቃል።

ቡድኑ ጠንካራ የአካላዊ ፍልሚያ እንደሚኖረው በሚጠበቀው በነገው ጨዋታ ባለፉት አራት መርሐ-ግብሮች አምስት ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረቱን ጥንካሬ ከማስቀጠል ባለፈ
በአንዳንድ ጨዋታዎች የሚታይበትን ያልታሰበ የመከላከል ድክመት በማረም ወደ ቦታው መመለስ ይጠበቅበታል።

ሲዳማ ቡና ከአስራ ስድስት የጨዋታ ሳምንታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከታታይ ድሎችን አስመዝግቦ ወጥ ካልነበረው ጉዞ በማገገም ራሱን
በሰንጠረዡ አካፋይ ላይ አደላድሏል።

ሦስት ተከታታይ ድሎች በማስመዝገብ በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው ቡድኑ በሁለቱም የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች የነበሩበትን ክፍተት በመጠኑ ማሻሻሉም ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ ነጥብ እና ደረጃውን ሽቅብ አሳድጓል። ዘጠኝ ነጥቦች በተገኙባቸው ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ግብ አለማስተናገዱ ደግሞ ከወገብ በታች የነበረበት የመከላከል መዋቅር እንደተሻሻለ ይጠቁማል። ቡድኑ ባለፉት ሁለት መርሐ-ግብሮች በተከታታይ ቢያሸንፍም በመጠኑ ጠንከር ያለ ፍልሚያ አሳልፎ ነበር። በጨዋታው ቢፈተንም ግን የሊጉን መሪ በመከተል ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ ቡናና ባህርዳር ከተማ ላይ ያሳካቸው ድሎች በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ የሚያመላክት ነው።

በነገው ወሳኝ ፍልሚያ ከተጋጣሚው አቀራረብ አንፃር የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ወደ ራሱ በማድረግ ሊጫወት እንደሚችል ሲጠበቅ የመስመር ተጫዋቾቹ ብቃት ደግሞ ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ እንዲወጣ እንደሚያስችሉት ይገመታል። ሆኖም  ከተከላካይ ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን የመከላከል ብቃቱን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጥበቅ ይገባዋል፤  ይህ ካልሆነ ግን ራሱን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል።

ሀዋሳ ከተማዎች በአወዳዳሪው አካል እገዳ ከተጣለበት እስራኤል እሸቱ ውጭ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የምያጡት ተጫዋች የለም። በሲዳማ ቡና በኩል ብርሀኑ በቀለ በቅጣት ካለመኖሩ በቀር ሁሉም የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።

ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም በ29 ጨዋታዎች ተገናኝተው ሁለቱም 10 ጨዋታዎች በእኩሌታ ስያሸነፉ  ቀሪዎቹ 9 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በጨዋታዎቹ በድምሩ 61 ኳሶች መረብ ላይ ሲያርፉ ሲዳማ 33 ሀዋሳ ደግሞ 27 ጎሎች አስቆጥረዋል።በጨዋታዎቹ በድምሩ 61 ኳሶች መረብ ላይ ሲያርፉ ሲዳማ 32 ሀዋሳ ደግሞ 29 ጎሎች አስቆጥረዋል።