ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተካሄደው ተጠባቂው ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ በሳምንቱ የመጨረሻ የሆነው የምሽቱ መርሐግብር ሀዋሳ ከተማን ከሲዳማ ቡና አገናኝቷል። ሀዋሳ ከተማዎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከአሸነፉበት አሰላለፍ ምንም አይነት የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ሲገቡ በተቃራኒው ሲዳማ ቡናዎች ኢትዮጵያ ቡናን ካሸነፉበት ስብስብ የስድስት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ ቶማስ ኢካራ፣ ጊት ጋትኮች፣ ብርሃኑ በቀለ፣ መስፍን ታፈሰ፣ ሬድዋን ናስር እና አስቻለው ሙሴን በማሳረፍ በምትካቸው መስፍን ሙሴ፣ ደግፌ አለሙ፣ ደስታ ደሙ፣ ያሬድ ባየህ፣ አበባየሁ ሀጂሶ እና ሳሙኤል ሳሊሶን ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በ26ኛ ሳምንት መርሐግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከመመራት ተነስተው 2-1 በማሸነፍ ጣፋጭ ድል የተቀናጁት ሀዋሳ ከተማዎች ያንኑ ድል ለማስቀጠል የኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ ተፋላሚ መሆኑን ካረጋገጠው ሲዳማ ቡና ጋር ተጠባቂ ጨዋታቸውን ለማድረግ በዝናባማው ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታድየም ተገኝተዋል። በበርካታ ደጋፊዎች ህብረ ዜማ ታጅቦ በዋና ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘሁ የተጀመረው ይህ ተጠባቂ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የሆነ የኳስ እንቅስቃሴን ያስመለከተን ጨዋታ ነበር።

የመጀመሪያውን 20 ያክል ደቂቃዎች በማጥቃቱ እና በጎል ማግባት ፍላጎት ረገድ ሀዋሳ ከተማዎች የተሻሉ ነበሩ። በቁጥር በዛ በማለት ከመሀል ከሚነሱ ኳሶች አሊያም ፈጣን አጥቂዎቻቸውን ዒላማ ያደረገ ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ረጃጅም ኳሶች ግብ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በተመሳሳይ ከ20ኛው ደቂቃ በኋላ ጨዋታውን በመቀየር ሲዳማ ቡናዎች በኳስ እንቅስቃሴም ሆነ በቁጥር በዛ ብሎ በማጥቃቱ ረገድ ብልጫ መውሰድ የቻሉ ቢሆንም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይሄ ነው የሚባል ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያስመለክተን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ክለቦች ለማሸነፍ ወደ ሜዳ የተመለሱ ሲሆን የሐዋሳ ቀዝቃዛ አየር ባልበገራቸው ደጋፊዎች ታጅቦ ሲቀጥል  ቡድኖች ኳስን የሜዳው መሀል ክፍል ላይ በማደራጀት ወደ ፊት በቁጥር በዛ ብለው በተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል። ወደ ግብ በመጠጋት ረገድ በአንፃሩም ቢሆን ተሽለው የቀረቡት ሲዳማ ቡናዎች 61ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ታደሰ ከሳጥኑ ውጭ በመሆን በሀይል አክርሮ የመታው ኳስ ለጥቂት በግቡ አግዳሚ በኩል ወጥቶበታል።

የመጀመሪያ ጥሩ የሚባል ሙከራቸውን ባደረጉ ብዙም ሳይቆይ ከ3 ደቂቃዎች በኋላ ሲዳማ ቡናዎች መሪ የሆኑበትን ግብ ማግኘት ችለዋል። 64ኛው ደቂቃ ላይ መነሻውን ከቀኝ መስመር አድርጎ የተሻማውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ በግንባሩ መጭረፍ የቻለ ሲሆን ያንን ኳስ ያገኘው እና በተከታታይ ጨዋታዎች ግቦችን በማስቆጠር ወጥ የሆነ አቋሙን ያስመለከተን ፍቅረኢየሱስ ተወልደብርሃን ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ከማዕዘን ተሻምቶ ማይክል ኦቱሉ ወደ ግብ የገጨውን ኳስ የሲዳማ ቡናው ተከላካይ ያሬድ ባየህ በእጅ በመነካቱ ምክንያት ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት የቡድኑ አምበል በረከት ሳሙኤል ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ሲዳማ ቡናዎች በደቂቃዎች ልዩነት ያጡትን መሪነት ለማስመለስ ይበልጥ ጫና ፈጥረው በቁጥር በመብዛት ለማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም ግን በተክለ ሰውነት ግዙፍ የሆኑትን የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮችን ማለፍ ተስኗቸው ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።