ቡናማዎቹ እና ነብሮቹ የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ የዕለቱ ሁለተኛ መርሐ-ግብር ነው።
በአርባ ሁለት ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጨረሻው መርሐ-ግብር ድሬዳዋ ከተማ ላይ ያሳኩት ድል ማስቀጠል በዋንጫ ፉክክሩ እንዲቆዩ ይረዳቸዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ሰሞነኛ ችግር በውጤት ረገድ ያለው የወጥነት ድክመታቸው ነው። ቡድኑ በእንቅስቃሴ ደረጃ ያለው ብቃት የከፋ ባይሆንም ከሰባት ሳምንታት ሽንፈት አልባ ጉዞ በኋላ በተከናወኑ አራት መርሐ-ግብሮች ላይ ተከታታይ ነጥብ ለማስመዝገብ ተቸግሯል። ለዚህ እንደ ምክንያትነት የሚጠቀሰው ደግሞ በግብ ማስቆጠር ረገድ ያለው ድክመት ሲሆን በአፈፃፀም በኩል ያለው ክፍተትም ከቡድኑ ውጤት መዋዥቅ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። ቡድኑ ጥሩ በተንቀሳቀሰባቸው ጨዋታዎች ጭምር በሚፈለገው መጠን ግብ አለማስቀጠሩም የዚህ ማሳያ ሲሆን የግብ ማስቆጠር ኃላፊነቱ በውስን ተጫዋቾች ጫንቃ ላይ መሆኑ ደግሞ በሚፈጠሩት ዕድሎች ልክ ግቦች እንዳይቆጠሩ አድርጎታል። ይህንን ተከትሎ ቡድኑ ካስቆጠራቸው ሀያ ሁለት ግቦች ውስጥ አስራ ስድስቱን ካስቆጠሩት አንተነህ ተፈራ እና ኮንኮኒ ሀፍዝ በተጨማሪ ሌሎች ተጫዋቾችም ኃላፊነቱን እንዲጋሩ የሚያስችል ስራ መስራት ከአሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ የሚጠበቅ የቤት ስራ ነው።
በሰላሣ ስምንት ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደረጃቸውን ለማሻሻል በአራት ነጥብ ልቀው 3ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ቡናማዎቹ ይፋለማሉ።
ነብሮቹ ዘለግ ላሉ የጨዋታ ሳምንታት በእንቅስቃሴም ይሁን በውጤት ረገድ ከታየባቸው መጠነኛ መቀዛቀዝ አገግመዋል፤ ቡድኑ ከ21ኛ እስከ 25ኛ ሳምንት በተከናወኑ ጨዋታዎች ካገኛኘው ነጥቦች እና ካስቆጣራቸው ግቦች የሚልቅ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ማግኘቱም እንደማሳያ መጥቀስ ይቻላል። ከዐፄዎቹ ጋር ነጥብ በተጋሩበት የመጨረሻው መርሐ-ግብር ላይ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ከተወሰደባቸው ብልጫ አገግመው በሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ የተሻለ በመንቀሳቀስ ጥቂት የማይባሉ ዕድሎች የፈጡሩት ነብሮቹ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ የነበራቸው የማጥቃት ጥንካሬ በነገው ወሳኝ ጨዋታ ላይ መድገም የሚጠበቅባቸው ሲሆን በጨዋታው ጅማሮ ያሳዩት ተጋጣሚ በርከት ያሉ ሙከራዎች እንዲያደርግ የፈቀደ የደከመ የመከላከል እንቅስቃሴ ግን መታረም የሚገባው ጉዳይ ነው።
ሁለቱም ቡድኖች በተገናኙባቸው 11 ግንኙነታቸው ነብሮቹ 5 ቡናማዎቹ ደግሞ 4 ጊዜ ስያሸንፉ በሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። ከተቆጠሩት 21 ጎሎች ደግሞ ሀድያ ሆሳዕና 11 ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ 10 ግቦችን አስቆጥረዋል።