የሁለት ቡድኖች ተጫዋቾች በደመወዝ አለመከፈል ለችግር መዳረጋቸውን ገለፁ

የሁለት ቡድኖች ተጫዋቾች በደመወዝ አለመከፈል ለችግር መዳረጋቸውን ገለፁ

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ላይ እየተካፈሉ የሚገኙት የአርባ ምንጭ እና ሀምበርቾ ተጫዋቾች በደመወዝ አለመከፈል ችግር ውስጥ መግባታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ2017 የውድድር ዘመን ላይ እየተወዳደሩ ካሉ ክለቦች መካከል የሆኑት አርባምንጭ ከተማ እና ሀምበርቾ በደመወዝ አለመከፈል የተነሳ ለችግር መዳረጋቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ጠቁመዋል። በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ31 ነጥቦች ስምንተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት በአሰልጣኝ አዱኛ ገላና የሚመሩት አርባምንጭ ከተማዎች ለአምስት ወራት ያህል ማግኘት የነበረባቸውን ከክለቡ ጋር የተስማሙበትን ወርሃዊ ደመወዝ ባለማግኘታቸው ለችግር መዳረጋቸውን በዝርዝር ለዝግጅት ክፍላችን ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የተቀመጠው እና ከሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው ሀምበርቾ ተጫዋቾችም በተመሳሳይ ከስድስት ወራት በላይ ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው በመጠቆም ከደመወዝ ጥያቄ ተጨማሪ የግል ጥቅማጥቅሞችም አለማግኘታቸው ለከፍተኛ ችግር እንደዳረጋቸው ገልፀዋል።

የሁለቱ ቡድኖች ተጫዋቾች ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥያቄያቸው መልስ እንዲያገኝ ደብዳቤ አስገብተዋል።