የጣና ሞገዶች ከመመራት ተነስተው የሊጉን መሪ ኢትዮጵያ መድንን 2-1 ማሸነፍ ችለዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት መርሐግብር ረቡዕ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት ነገር ግን በነበረው የአየር ንብረት ምክንያት እና በአንዳንድ ጉዳዮች ተራዝሞ ዛሬ እንዲካሄድ የተወሰነው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድንን ከ ባህር ዳር ከተማ ጋር አገናኝቷል። ኢትዮጵያ መድኖች ባሳለፍነው ሳምንት አርባምንጭ ከተማን ድል ካደረጉበት አሰላለፍ አለን ካይዋን በ ረመዳን የሱፍ ቀይረው ሲገቡ በተመሳሳይ ባህር ዳሮች ግርማ ዲሳሳ ፣ ፍፁም አለሙ እና አቤል ማሙሽን በማሳረፍ በምትካቸው ወንድሜነህ ደረጀ፣ ፍሬው ሰለሞን እና ጄሮም ፍሊፕ በማስገባት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
በሊጉ አንደኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ክለቦች ያገናኘው ጨዋታ ተጠባቂ ነበር። ሁለት ተመሳሳይ ጨዋታን የሚጫወቱ ቡድኖች ከመሆናቸው አንፃር ጥሩ እና ሳቢ እግርኳስን የተመለከትንበት ነበር። በእንቅስቃሴ እና በኳስ ፍሰቱ ተመጣጣኝ የሚባል እንቅስቃሴን ያስመለከቱን ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ኳስን ከራሳቸው ግብ መስርተው በመውጣት ሲጫወቱ ተስተውሏል። 17ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ መድኖች መሪ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ወገኔ ገዛኸኝ ከሜዳው የመሃል ክፍል አካባቢ በመሆን ያቀበለውን ኳስ ረመዳን የሱፍ ወደ ሳጥን በመግባት የመታውን ኳስ ከመረብ ላይ አሳርፎ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ ባህር ዳር ከተማዎች በኳስ እና በተጫዋች ቁጥር ብልጫ በመውሰድ ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ግብ ለማግኘት ጥረት ማድረግ የቻሉ ሲሆን የግብ ብልጫቸውን ለማስጠበቅ በቁጥር ወደ ራሳቸው ግብ ጥቅጥቅ ብለው የሚከላከሉትን የመድን ተጫዋቾች አልፎ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው 1-0 በሆነ ውጤት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ የተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ፍሬው ሰለሞን እና ጄሮፕ ፊሊፕን በማስወጣት ፍፁም አለሙ እና ሙጂብ ቃሲምን በማስገባት ወደ ሜዳ የተመለሱት ባህር ዳር ከተማዎች ቅያሪያቸው ውጤታማ መሆኑን ያሳዩበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 51ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ይበልጣል ከተከላካይ ጀርባ ያሻገረለትን ኳስ ወንድወሰን በለጠ አቁሞ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ሙጂብ ቃሲም ወደ ግብ በመቀየር መድኖች ለተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ያስከበሩትን ግብ መድፈር ችሏል።
የሚያገኟቸውን ኳሶች ፈጣን በሆነ ሽግግር ወደ ተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል ይዘው የሚገቡት ኢትዮጵያ መድኖች 62ኛው ደቂቃ ላይ መነሻውን ከቀኝ መስመር ያደረገው ኳስ ረመዳን የሱፍ በጥሩ ሁኔታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ወገኔ ገዛኸኝ ወደ ግብ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ በሚገርም ብቃት መልሶበታል። የጨዋታው መደበኛ ሰዓት ሊጠናቀቅ አስር ያክል ደቂቃዎች ሲቀሩት ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ባህር ዳር ከተማዎች ያለቀላቸው እና መሪ መሆን የሚችሉባቸውን ሁለት የግብ ሙከራዎችን በቸርነት ጉግሳ እና በሙጂብ ቃሲም አማካኝነት ማድረግ ቢችሉም በግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ተጋድሎ አማካኝነት ግብ ከመሆን ታድጓቸዋል።
መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ የባከኑ ጭማሪ ደቂቃዎች ወደ መጠናቀቁ ተቃርቦ የዳኛ ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት ባህር ዳሮችን በደስታ ስሜት ውስጥ የከተተ ጎል ማስቆጠር ችለዋል። 90+3′ ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ ጥሩ በሆነ እይታ ያቀበለውን ኳስ በእድሜ ትንሹ እና ታዳጊው ሄኖክ ይበልጣል የግል ችሎታውን አንፀባርቆ ባሳየት መንገድ የመድን ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ በውድድር አመቱ የመጀመሪያውን ግብ በማስቆጠር ክለቡን ከመመራት ተነስቶ ጣፋጭ ድል እንዲያሳካ ምክንያት መሆን ችሏል።
ይህንንም ተከትሎ በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመሩት ባህር ዳር ከተማዎች የሊጉ መሪ የሆነውን ኢትዮጵያ መድን ከዘጠኝ ተከታታይ ጨዋታዎች በኋላ 2-1 በማሸነፍ እጅ እንዲሰጥ ማድረግ ችለዋል።