ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ድሬዳዋ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ድሬዳዋ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ

በተመሳሳይ ነጥብ በግብ ክፍያ የሚበላለጡ በደረጃ ሰንጠረዡ ተከታትለው የተቀመጡት ብርቱካናማዎቹ እና ምዓም አናብስት የሚያደርጉት ፍልምያ ለሁለቱም ቡድኖች ካለው አስፈላጊነት ተጠባቂ ነው።

ሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች አስተናግደው በሀያ ዘጠኝ ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች የቅርብ ተፎካካሪያቸው በሚገጥሙበት ትልቅ ትርጉም ያለው የነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማስመዝገብ እጅግ አስፈላጊያቸው ነው።

በ27ኛ ሳምንት ፋሲል ከነማን ካሸነፈ በኋላ በተደረጉ ጨዋታዎች ድል ማሳካት ያልቻለው ድሬዳዋ ከተማ በሁለተኛው ዙር የመጀመርያ ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ድል፣ ሦስት አቻና አንድ ሽንፈት በማስተናገድ መጠነኛ መሻሻል ሲያሳይ ቆይቶ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች በገጠሙት ሽንፈቶች አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። በመደዳ ከገጠማቸው ሽንፈቶች ለማገገም ወደ በሚገቡበት የነገው ጨዋታም በርከት ያሉ ድክመቶቻቸውን አርመው መቅረብ ይኖርባቸዋል። የውድድር ዓመቱን ሙሉ በሚባል ሁኔታ ቡድኑን ዋጋ ሲያስከፍለው የነበረው የግብ ማስቆጠር ድክመትም ከምንም ነገር በፊት ሊቀረፍ የሚገባው ችግር ሲሆን ከተከታታይ ሽንፈቶቹ በፊት በተካሄዱ ስድስት መርሐ-ግብሮች ሦስት ግቦች ብቻ አስተናግዶ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ያስተናገደው የኃላ ክፍሉም ሌላው መሻሻል የሚገባው የቡድኑ ክፍል ነው።

ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረ ቡድን በሚገጥምበት የነገው ጨዋታ በመከላከል ረገድ ትልቅ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ባይገመትም በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለው የማጥቃት ክፍሉን ማስተካከል ግን የረዳት አሰልጣኝ ተረፈ ሂርጻሳ ትልቁ የቤት ስራ ነው።

ከነገው ተጋጣሚያቸው ድሬዳዋ ከተማ ጋር ተመሳሳይ ሀያ ዘጠኝ ነጥብ ሰብስበው 15 ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች በ25ኛ ሳምንት ሀድያ ሆሳዕና ላይ ያሳኩት ድል በመድገም ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ ተብሎ ይታመናል። 

በሁለተኛው ዙር በተከናወኑ ዘጠኝ ጨዋታዎች ስድስት ሽንፈት፣ ሁለት ድልና አንድ የአቻ ውጤት  ያስመዘገበው መቐለ 70 እንደርታ ከአምስት ቀናት በፊት ዋና አሠልጣኙን ከመንበሩ አንስቷል። የአሠልጣኝ ለውጡ የተደረገበት ጊዜ ብዙዎችን እያከራከረ ቢገኝም በዚህ የውድድር ዓመት ወልዋሎን ያሰለጠኑት አንጋፋው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም በቦታው ተሹመዋል። አዲሱ አሠልጣኝ ቡድኑ በየዲፓርትመንቱ ያለበትን ችግር በዚህች አጭር ጊዜ አሻሽለው ለመቅረብ አዳጋች ቢሆንም በዋናነት በማጥቃቱ እንዲሁም መከላከሉ ላይ ያለውን ውስንነት ትኩረት ሰጥተው ያስተካክላል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይም በሊጉ ከአዳማ ከተማ እና ወልዋሎ በመቀጠል ብዙ ግብ ያስተናገደው እና በቅርብ ሳምንታት በርከት ያሉ ግለ-ሰባዊ ስህተቶች የተስተዋሉበት የመከላከል አደረጃጀቱ በቀዳሚነት መስተካከል የሚገባው ክፍል ሲሆን ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጥረው የፊት መስመር ጥምረትም ጉልህ የአፈፃፀም ድክመቱን ማረም ይኖርበታል።  

በወራጅ ቀጠናው የሚገኙት ብርቱካናማዎቹ እና ምዓም አናብስት በሊጉ ያላቸው ዕቅድ ተመሳሳይ ነው። የነገው ጨዋታም ሁለቱም በተመሳሳይ
በሊጉ ለከርሞ ለመጫወት የሚያስችላቸውን ነጥብ ለመሰብሰብ የሚያደርጉት ትልቅ ትርጉም ያለው ጨዋታ እንደመሆኑ ፍልምያው ተጠባቂ ነው።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ካለው መሐመድኑር ናስር ውጭ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም። በመጨረሻው ጨዋታ በቅጣት ምክንያት ያልተሰለፈው አቡበከር ሻሚልም ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ነው። በመቐለ 70 እንደርታ በኩል አምበሉ ያሬድ ከበደ በሕመም ምክንያት አይሰለፍም፤ ጉዳት ላይ የሰነበቱት ሔኖክ አንጃው እና ቦና ዓሊ ደግሞ ልምምድ ቢጀምሩም በነገው ጨዋታ የመሳተፋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስከ አሁን 6 ጊዜ ሲገናኙ ምዓም አናብስት 4 ጊዜ በማሸነፍ ብልጫውን ሲይዙ ብርቱካንማዎቹ በአንፃሩ 2 ድል አስመዝግቧል። በግንኙነታቸውም ሞዓም አናብስቱ 9 ብርቱካናማዎቹ በበኩላቸው 6 ጎሎችን መረብ ላይ አሳርፈዋል።