ሪፖርት | ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ የተደረገው ፍልሚያ አቻ ተጠናቋል

ሪፖርት | ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ የተደረገው ፍልሚያ አቻ ተጠናቋል

በሊጉ ለመቆየት ትልቅ ትርጉም የነበረው የድሬዳዋ ከተማ እና መቐለ 70 እንደርታ ጨዋታ 1-1 ተቋጭቷል።።

ተከታታይ ሽነፈት እያስተናገዱ ያሉት ድሬደዋ ከተማዎች ከባለፈው ስብስባቸው የስድስት ተጫዋቾች ቅያሪ አድርገዋል። ቴዎደወሮስ ሀሙ፣ መስዑድ መሐመድ፣ ሄኖክ ሀሰን፣ አቤል አሰበ፣ ሐቢብ ከማል እና ሙኸዲን ሙሳን አሳርፈው አህመድ ረሺድ፣ አቡበከር ሻሚል፣ አስራት ቱንጆ፣ ድልአዲስ ገብሬ፣ ዮሐንስ ደረጄ እና አቡበከር ወንድሙ ተክተው ሲገቡ በአንፃሩ መቐለ 70 እንደርታዎች በአዲሱ አሰልጣኛቸው እየተመሩ ባለፈው ነጥብ ከተጋሩበት አሰላለፍ ያሬድ ከበደ እና አሸናፊ ሐፍቱን አሳርፈው ኪሩቤል ኃይሉ እና መድሃኔ ብርሃኔን ወደ ሜዳ ይዘው ገብተዋል።

ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ማኑሔ ወልደፃድቅ በቅርቡ በድንገተኛ ህመም ምክንያት ህይወቱ ላለፈው ጋናዊው አማካይ ጋብሬል አህመድ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ ጨዋታውን አስጀምረውታል። ሙከራ ለመመልከት በርካታ ደቂቃዎችን በማስጠበቅ ፈዛዛ እንቅስቃሴን ያሳየን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በጨዋታው ለጎል የቀረበ ሙከራ የተመለከትነው በ15ኛው ደቂቃ ነበር። ድሬዎች ከመሐል ሜዳ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን አጥቂው ዮሐንስ ደረጄ ነፃ ኳስ አግኝቶ በግቡ አናት ለጥቂት የወጣበት የሚጠቀስ ነበር።

ወደ እንቅስቃሴው ለመግባት ደቂቃ የወሰደባቸው መቐለ 70 እንደርታዎች ሃያ አምስተኛው ደቂቃ ላይም በጨዋታው የመጀመርያ ሙከራቸውን ወደ ጎልነት ቀይረውታል። ብሩክ ሙሉጌታ የግል ብቃቱ ተጠቅሞ ከቀኝ መስመር ኳሱን እየገፈ ተጫዋች ታግሎ በማለፍ በጥሩ ሁኔታ ወደ ውስጥ የላከውን ከጎል እርቆ የሰነበተው ያሬድ ብርሃኑ አስቆጥሮታል።

በተደጋጋሚ ሽንፈት ምክንያት ጫና የገቡ የሚመስሉት ብርትካናማዎቹ ከወትሮ ከሚታወቁበት የጨዋታ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዘው የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያደርጉት ጥረት ኳሶቻቸው እየተቆራረጡ ምንም ሙከራ ሳያደርጉ ሲቀሩ በአንፃሩ መቐለ 70 እንደርታዎች 38ኛው ደቂቃ ላይ ኪሩቤል ኃይሉ ከቅጣት ምት ካደረገው ሙከራ በቀር አልፎ አልፎ የተሻሉ የጎል አጋጣሚዎችን ለማግኘት ከሚደረግ ሂደት ውጭ አመዛኙን በጥንቃቄ ተጫውተው አጋማሹን 1-0 እየመሩ ወጥተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ያሬድ ብርሃኑ ከግራ መስመር ይዞት የገባውን ወደ ውስጥ የላከውን እና መድኃኔ ብርሃኔ እና አብዱልሰላም የሱፍ ሳጥን ውስጥ ኳሱን ለማሸነፍ በሚደረግ ትግል አብዱልሰላም ራሱ ላይ ለማስቆጠር ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም አውጥቶታል።

የተጫዋች ለውጥ በማድረግ ከአጋማሹ በተሻለ ሁኔታ ወደ ጨዋታው ለመመለስ በሙሉ አቅማቸው በተለይ በሁለቱም መስመሮች በኩል ሰብረው ለመግባት ተደጋጋሚ ጥረት ያደረጉት ብርትካናማዎቹ ከብዙ ደቂቃ መጠበቅ በኋላ በ71ኛው ደቂቃ ላይ ቤንጃሚን ኮቴ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሀቢብ ከማል ወደ ጎልነት ቀይሮታል።

የአቻነት ጎል ከተቆጠረ በኋላ የጨዋታው ግለት ከፍ ብሎ ሲቀጥል ብርትካናማዎቹ የበላይነትን በወሰዱበት ሁኔታ በ81ኛው ደቂቃ መቐለ 70 እንደርታዎች እጅግ ለጎል የቀረበ አጋጣሚ አግኝተዋል። ከቀኝ መስመር መድሀኔ ብርሃኔ በግራ እግሩ ወደ ውስጥ ያሻማውን የድሬዎቹ ተከላካይ አህመድ ረሺድ ኳሱን በግንባሩ ለማውጣት ወደ ራሱ የግብ ክልል መቶት የነበረውን ግብ ጠባቂው አላዛር መረነ ጎል እንዳይቆጠርባቸው አድርጓል።

በቀሪ የመጨረሻ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ለማግኘት ቢታትሩም የተለየ ነገር ሳያስመለክቱን ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።