ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | መቐለ 70 እንደርታ ከ ስሑል ሽረ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | መቐለ 70 እንደርታ ከ ስሑል ሽረ

በወራጅ ቀጠናው የሚገኙት መቐለ 70 እንደርታ እና
ስሑል ሽረ በሊጉ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ነጥብ ለማግኘት የሚፋለሙበት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።

በሰላሣ ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች በሊጉ ለመቆየት ወሳኝ ከሆኑ ስድስት መርሐግብሮች ውስጥ አንዱ የሆነውን ጨዋታ ነገ ያደርጋሉ።

ምዓም አናብስት ድል ካደረጉ አምስት የጨዋታ ሳምንታት አስቆጥረዋል፤ ቡድኑ በመጀመርያው ዙር የመጨረሻ ሰባት ሳምንታት ውስጥ አንድ ሽንፈት ብቻ በማስተናገድ ደረጃውን ካሻሻለ በኋላ በሁለተኛው ዙር ደካማ ውጤት ማስመዝገቡን ተከትሎ ወራጅ ቀጠናው ውስጥ ገብቷል። ከውድድር ዓመቱ አጋማሽ በኋላ በተካሄዱ አስራ አንድ ጨዋታዎች ውስጥ ሰባት ሽንፈት፣ ሁለት ድል እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት ምዓም አናብስት በተለይም በሀዋሳ ቆይታቸው ያስመዘገቡት ደካማ ውጤት አሁን ላሉበት ደረጃ ምክንያት ነው።

ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚያደርጉት ጉዞ ወሳኝ በሆነው ጨዋታ ሌላው ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሞት ሽረት ትግል ማድረግ የሚጠበቅበትን ስሑል ሽረ የሚገጥሙት መቐለዎች በነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ማግኘት ከቻሉ በ14ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ማጥበብ ይችላሉ። ከነገው ጨዋታ ውጤት ማግኘት መቻል ደግሞ ለቡድኑ ከውጤትም በላይ ፋይዳ ይኖረዋል። በውድድሩ ከቀሩት መርሐግብሮች አንጻር ሲተያይ በቀሪ ጨዋታዎች ልክ እንደ ዋንጫ ጨዋታ መፋለም የሚጠበቅባቸው ምዓም አናብስት ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ከምንም በላይ የማጥቃት አጨዋወታቸውን ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል። በ25ኛው ሳምንት ሀድያ ሆሳዕናን ሁለት ለባዶ ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ በተከናወኑ አምስት መርሐግብሮች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጥረው ቡድኑ በነገው ጨምሮ ቀጥለው በሚካሄዱ አምስት ወሳኝ መርሐግብሮች የፊት መስመሩን የጥራት ደረጃ ከፍ ማድረግ ይኖርበታል።

በሀያ ሁለት ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ስሑል ሽረዎች በሊጉ ለመቆየት ያላቸውን እንጥፍጣፊ ዕድል ለማለምለም ድልና ድልን ብቻ እያለሙ ወደ ሜዳ መግባት ይኖርባቸዋል።

በሀዋሳ የስምንት ሳምንታት ቆይታቸው ሰባት አቻ እና አንድ ሽንፈት ያስመዘገቡት ስሑል ሽረዎች አሁንም ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ከማጠናቀቅ ድክመታቸው መላቀቅ አልቻሉም። ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ስድስት መርሐ-ግብሮች በመደዳ ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ እንዲሁም በሊጉ በአስራ ሦስት ጨዋታዎች ላይ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ቀዳሚ መሆኑም የዚህ ማሳያ ነው። በሊጉ ከወልዋሎ፣ አዳማ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ጋር ቀጥለው ከነገው ተጋጣሚያቸው መቐለ ጋር በጣምራ በርከት ያሉ ሽንፈቶች በማስተናገድ 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ስሑል ሽረዎች ባለፉት ስድስት የጨዋታ ሳምንታት ከሽንፈት መራቃቸው እንደ አወንታ የሚጠቀስላቸው ነጥብ ቢሆንም በውድድሩ ወሳኝ ወቅት ላይ ድል ማድረግ ባለመቻላቸው ደረጃቸውን ማሻሻል አልቻሉም።

ፕሪምየር ሊጉ ሊጠናቀቅ የስድስት ጨዋታዎች ዕድሜ በቀረበት ጊዜ ላይ በሊጉ ለመቆየት ከሚያስችለው 14ኛ ደረጃነት በአስራ ሁለት ነጥቦች ለመራቅ የተገደዱት ሽረዎች ከቀሩት መርሐ-ግብሮች እና ካለው የነጥብ ልዩነት አንፃር ሲተያይ በሊጉ የመቆየታቸው ዕድል አጠያያቂ ቢሆንም ቡድኑ ያሳየውን አንፃራዊ መሻሻል ወደ ድል መመንዘር ከቻለ ግን ዕድሉን ማለምለም የሚችልበት ጠባብ ዕድል አለው።

በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ በቅጣት ቤንጃሚን ኮቴ ደግሞ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ አምበሉ ያሬድ ከበደ ግን አገግሞ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል። ስሑል ሽረዎች ከጉዳት እና ከቅጣት ነፃ የሆነ ስብስባቸውን ይዘው ለነገው ጨዋታ ይቀርባሉ።

ቡድኖቹ ከተሰረዘው እና በመቐለ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የ2012 ጨዋታ ውጭ በፕሪምየር ሊጉ 3 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ሁለቱም ቡድኖች በእኩሌታ አንድ አንድ ጨዋታ ድል ሲያደርጉ የተቀረው አንድ ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። መቐለ 70 እንደርታ 3 ግቦች ስያስቆጥር ስሑል ሽረ 2 ግቦች አስቆጥሯል።