ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | መቐለ 70 እንደርታ ከ ፋሲል ከነማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | መቐለ 70 እንደርታ ከ ፋሲል ከነማ

ምዓም አናብስት ከወራጅ ቀጠናው የሚወጡበት ዕድል ለማመቻቸው ዐፄዎቹ ደግሞ ከስጋት ቀጠናው ለማምለጥ የሚፋለሙበት ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል ፤ በቡድኖቹ መሐል የአራት ነጥብ ልዩነት ብቻ መኖሩም መርሐ-ግብሩ ተጠባቂ ያደርገዋል።

በሰላሣ ሦስት ነጥቦች 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ከወራጅ ቀጠናው የሚወጡበትን ዕድል ለማመቻቸት የሚያስችላቸውን ድል ለማስመዝገብ ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ነገ ያደርጋሉ።

ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ስሑል ሽረን መርታት የቻሉት ምዓም አናብስት በአዕምሮ ደረጃ ይህ ጨዋታ የሰጣቸውን የማሸነፍ ሥነ ልቦና ማስቀጠል መቻል ዋነኛ የነገ ጨዋታቸው መሰረት ነው። ድሉ ከሦስት ነጥብ ባለፈ ቡድኑ በተከታታይ ጨዋታዎች ያለ ሙሉ ነጥብ የሚወጣበትን መንገድ የቀየረ መሆኑ ሲታሰብ በአእምሮ ረገድ የሚሰጠው ዋጋ ትልቅ ሊሆን ይችላል። ሆኖም የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም ተከታዩ አዳማ ከተማ በዚህ የጨዋታ ሳምንት ድል ማድረጋቸው ተከትሎ በሊጉ የሚቆይበትን ዕድል ለማለምለም በአራት ነጥብ እና በአንድ ደረጃ ከፍ ብሎ የተቀመጠውን የነገ ተጋጣሚውን ፋሲል ከነማ መርታት ይኖርበታል።

ከነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ይዞ ለመውጣትም በተከታታይ አምስት መርሐ-ግብሮች ያስቆጠረው ድምር የግብ መጠን በአንድ ጨዋታ በማስቆጠር ውስን መሻሻል ያሳየውን የማጥቃት አጨዋወቱን ጥራት ከፍ ማድረግ እንዲሁም በሊጉ ከወልዋሎ እና አዳማ በመቀጣል ከፍተኛው የግብ መጠን ያስተናገደውና የውድድር ዓመቱ ዋነኛ ድክመቱ ሆኖ የዘለቀው የመከላከል ክፍተቱም ማረም ይኖርበታል።

በሰላሣ ሰባት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ከድል ጋር መራራቃቸውን ተከትሎ ለስጋት ቀጠናው ይበልጥ ቀርበዋል።

ዐፄዎቹ ከ22ኛው እስከ 24ኛ ሳምንት ድረስ ካስመዘገቧቸው ሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ ነገሮች በአወንታ እየሄዱላቸው አይገኝም፤ በውጤትም ሆነ በእንቅስቃሴ ረገድ የሚስተዋልበት የወጥነት ችግርም የቡድኑ መገለጫ ሆኗል። ቡድኑ ስምንት ግቦች አስቆጥሮ እና ጥሩ ተንቀሳቅሶ በመደዳ ድል ካደረገባቸው ሦስት ጨዋታዎች በኋላ ሳይጠበቅ የገጠሙት ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች እንዲሁም አጠቃላይ የውድድር ዓመት ጉዞውም ጉልህ የወጥነት ችግር እንዳለበት ማሳያዎች ናቸው። ለዚህ እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለው ደግሞ በማጥቃቱ ረገድ ያለባቸው ተከታታይነት ያለው ብቃት የማሳየት ድክመት ሲሆን ቡድኑ በግቦች ተንበሽብሾ ድል ካድረገባቸው መርሐ-ግብሮች በኋላ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች አራት ግቦች ብቻ ማስቆጠሩ እንዲሁም ከተቆጠሩ ግቦች ውስጥ ሁለቱ ከፍፁም ቅጣት ምት የተገኙ መሆናቸውም ለወጥነት ችግሩ ሁነኛ ማሳያ ነው።

በውድድር ዓመቱ በጉዳት እየታመሱ እዚህ ከደረሱት ቡድኖች ውስጥ የሚጠቀሱት ዐፄዎቹ በ24ኛው ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ካሳኩት ድል በኋላ በሰባት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን ብቻ ማግኘት ችለዋል፤ የነገው ጨዋታም ቀስ በቀስ ራሳቸውን ለወራጅ ቀጠናው ቀርበው ያገኙት በመሆኑ ብያንስ የሁለት ደረጃ መሻሻል ለማግኘት ይህንን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም የናፈቃቸውን ድል ማግኘት እና ነጥባቸውን 40 ማድረስ ከዚህ ጨዋታ የሚፈልጉት የመጨረሻ ውጤት ቢሆንም ይህ እንዲሳካ ግን ንፁህ የግብ ዕድሎችን ደጋግሞ በመፍጠር እና በግብ ፊት ትክክለኛ ውሳኔ ወስኖ የማስቆጠር ችግራቸው ማረም ግድ ይላቸዋል።

በመቐለ 70 እንደርታ በኩል ኪሩቤል ኃይሉ በቅጣት ቤንጃሚን ኮቴ ደግሞ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው፤ ሙልጌታ ወልደጊዮርጊስ ግን ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።
በተደጋጋሚ ጉዳት እና ቅጣት እየታመሰ የሚገኘው ፋሲል ከነማ በነገው ጨዋታም በጉዳት እና ቅጣት በርከት ያሉ ተጫዋቾችን አያገኝም። ተከላካዮቹ እዮብ ማቲያስ እና ምኞት ደበበ አማካዩ አቤል እንዳለ እንዲሁም አጥቂው አማኑኤል ገብረሚካኤል በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ቅጣት ያለባቸው አማካዩ ሀብታሙ ተከስተ እና ማርቲን ኪዛም በቅጣት ነገ የማይኖሩ ይሆናል።

ሁለቱም ቡድኖች የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ ሳይጨምር በሊጉ 5 ጊዜ ሲገናኙ ሁለቱም በተመሳሳይ አንድ አንድ ጨዋታ ላይ ድል አድርገው በተቀሩት 3 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ሁለቱም ቡድኖች በእኩሌታ ሁለት ሁለት ግቦች አስቆጥረዋል።