የወራጅነት ስጋት ያለበትን መቐለ 70 እንደርታን ከፋሲል ከነማ ያገናኘው የምሽቱ ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
የ32ኛ ሳምንት መርሐግብር መዝጊያ ጨዋታ ያለመውረድ የሚታገለውን መቐለ 70 እንደርታን ድል ከራቀው ፋሲል ከነማ ጋር አገናኝቷል። መቐለ 70 እንደርታዎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በሊጉ መውረዱን ያረጋገጠውን ስሑል ሽረ 2-1 ካሸነፉበት አሰላለፍ ዘረሰናይ ብርሃነ፣ ሰለሞን ሐብቴ እና ኪሩቤል ሃይሉን በማሳረፍ በምትካቸው መናፍ ዐወል፣ ሄኖክ አዱኛ እና ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስን ሲያስገቡ በተመሳሳይ ፋሲል ከነማዎች ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት አሰላለፍ በቅጣት ጨዋታው የሚያልፈውን ሀብታሙ ተከስተን ጨምሮ ቢኒያም ጌታቸውን በማስወጣት አቤል እያዩ እና አንዋር ሙራድን ወደ ሜዳ አስገብተዋል።
ምሽት 12:00 ሲል በዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ መሪነት በሁለቱ ቡድኖች የተጀመረው ይህ ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታዎች ከተደቀነባቸው የመውረድ ስጋት ለመውጣት እንዲሁም ፋሲል ከነማዎች ለረጅም ሳምንታት ከተራራቁት ድል ጋር ለመታረቅ ብሎም ደረጃቸውን ለማሻሻል ለሁለቱም ቡድኖች እጅግ አስፈላጊ ጨዋታ ነው። በጨዋታው ጅማሮ በእንቅስቃሴ ረገድ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ያስመለከቱን ሲሆን ሙከራ በማድረግ ፋሲሎች ቀዳሚ ነበሩ 5ኛው ደቂቃ ላይ አንዋር ሙራድ ግብ ጠባቂውን በማለፍ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ራሱ ግብ ጠባቂው ሶፎንያስ ሰይፈ ወደ ውጭ አውጥቶበታል።
ወደ ግብ በፈጣን ሽግግር ደጋግመው መድረስ የቻሉት ፋሲሎች 17ኛው ደቂቃ ላይ ኪሩቤል ዳኜ በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ይዞት የመጣውን ኳስ አሻምቶ ጌታነህ ከበደ በግንባሩ ገጭቶ በግቡ ቋሚ ለጥቂት የወጣበት ኳስ አስቆጪ ሙከራ ነበር። መቐለዎች 23ኛው ደቂቃ ላይ ኢማኑኤል ሳባን ከፋሲል ተጫዋቾች ኳስ ነጥቆ ወደ መስመር በመጠጋት ያሻማውን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ በግንባሩ ቢገጨውም ለጥቂት በግቡ አግዳሚ ወጥቶበታል።
36ኛው ደቂቃ ላይ ሸሪፍ መሐመድ ከራሱ የግብ ክልል ሆኖ ወደ ግብ ለማሻማት የመታው ኳስ በግብጨጠባቂው የአቋቋም ስህተት ምክንያት ነጥሮ ቢያልፈውም እንደምንም ብሎ ከግቡ መስመር ላይ ተወርውሮ ወደ ውጭ አውጥቶታል። ይህም ለመቀሌዎች አስቆጪ የግብ ዕድል ነበር። ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ የተንቀሳቀሱ እና ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል በተደጋጋሚ የደረሱ ቢሆንም ግብ ሳያስመለክቱን የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት የግድ ግብ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን የተረዱት መቐለ 70 እንደርታዎች 52ኛው መሪ ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል። የፋሲል ከነማ ተጫዋች ለመቆጣጠር ያዳገተውን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ ወደ ፊት ገፍቶ በመሄድ ያሻገረውን ኳስ ቦና ዓሊ ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
የግቡ መቆጠር ይበልጥ መነቃቃት የፈጠረላቸው መቐለ 70 እንደርታዎች ድጋሚ ግብ ለማስቆጠር ብልጫ ወስደው በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ፋሲል ከነማዎች ድንገተኛ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 62ኛው ደቂቃ ላይ ከሜዳው የመሀል ክፍል ላይ ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ እዮብ ማቲያስ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።
መቐለዎች በእጃቸው የነበረውን ብልጫ መልሰው ለማስመለስ ጫና ፈጥረው መጫወት ቢችሉም በራሳቸው የግብ ክልል በቁጥር በዛ ብለው መከላከሉ ላይ ትኩረት ያደረጉትን የፋሲል ከነማ ተጫዋቾች አልፎ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ይህንንም ተከትሎ በደረጃው ሰንጠረዥ አፄዎቹ 13ኛ ላይ እንዲሁም ምዓም አናብስቶቹ ባሉበት 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።