ሪፖርት | ሐይቆቹ በግቦች ተንበሽብሸው ስሑል ሽረን ረተዋል

ሪፖርት | ሐይቆቹ በግቦች ተንበሽብሸው ስሑል ሽረን ረተዋል

27 ሙከራዎች በተደረጉበት በረፋዱ ሀዋሳ ከተማን ከስሑል ሽረ ባገናኘው ጨዋታ ስድስት ጎሎች ተቆጥረው ሀዋሳ ከተማ 5ለ1 ረምርሟል።

ረፋድ 3:30 ላይ የተደረገው የእለቱ ቀዳሚ ጨዋታ አስቀድመው ከሊጉ መውረዳቸውን ያረጋገጡትን ስሑል ሽረዎችን በጥሩ ተነሳሽነት ያለመሸነፍ ጉዟቸውን ካስቀጠሉት ከሀዋሳ ከተማዎች አገናኝቷል። ስሑል ሽረ በ32ኛው ሳምንት በፈረሰኞቹ 1ለ0 ሲረቱ ይዘው ከገቡት ቋሚ ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ነፃነት ገብረመድህንን በመሐመድ ሱሌይማን ተክተው ሲገቡ፤ሀዋሳ  ከተማ በተጠናቀቀው ጨዋታ ሳምንት መቻልን 3ለ1 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት የመጀመሪያ ቋሚ አሰላለፍ እንዲሁ የአንድ ተጫዋች ለውጥ አድርገው ቸርነት አውሽን በብሩክ ኤልያስ ተክተው ቀርበዋል።

ፈጣን ሽግግሮች በታዩበት በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ቡድኖች ቀዳሚ ለመሆን ጥረት ያደረጉበት ሆኖ ሲመዘግብ ሀዋሳ ከተማዎች ግልፅ የግብ እድል በመፍጠር ቀዳሚ መሆን ችለው ነበር፤ በ7ኛው ደቂቃ ላይ በተከላካይ ጀርባ አማኑኤል ጎበና የጣለውን ኳስ አሊ ሱሌይማን በፍጥነት ደርሶ የኳሱን አቅጣጫ ቀይሮ ግብ ጠባቂውን አልፎ ባዶ ግብ ላይ ቢገኝም አጋጣሚውን ሳይጠቀም ሲቀር ስሑል ሽረዎች በመልሶ ማጥቃት ገብተው መሪ ሆነዋል፤ በ9ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ኳስ ይዘው ሲገቡ ፋሲል አስማማው እና ክፍሎም ገብረህይወት ባደረጉት አንድ ለአንድ ቅብብል በጥሩ ሁኔታ ወደ ሳጥን አሻምተው ብርሃኑ አዳሙ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብነት ቀይሮታል።

ሳይጠብቅ ግብ የተቆጠረባቸው ሐይቆቹ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው በረጃጅም ኳሶች አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት የጠራ ሙከራ ባያደርጉም ወደ ፊት እየሄዱ ጎል ከተቆጠረባቸው ከአስር ደቂቃ በኋላ የአቻነት ግብ አግኝተዋል፤ በ19ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ አሊ ሱሌማን በቀኝ መስመር በኩል አግኝቶ ወደ ሳጥን አሻግሮ ተባረክ ሂፋሞ ከመረብ ጋር አገናኝቶታል።

በተደጋጋሚ በረጃጅም ኳሶች ግልፅ አጋጣሚዎችን ሲያገኙ የነበሩት ሐይቆቹ በ24ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብ የቀረበ አስቆጪ እድል አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፤ ተባረክ ሂፋሞ ከራሳቸው ሜዳ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ አሊ ሱሌይማን በፍጥነት ደርሶ ከግብ ጠባቂው ፊትለፊት ተገናኝቶ ወደ ግብ መጥቶ ግብ ጠባቂው ጨርፎ ያወጣባቸው አጋጣሚ ሌላኛው ወርቃማ እድል የነበረ ቢሆንም መጠቀም አልቻሉም።

ቡድኖቹ ልክ እንደመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወደ ፊት የመሄድ እንቅስቃሴያቸው እየተቀዛቀዘ ሲመጣ የተመለከትን ቢሆንም ስሑል ሽረዎች አልፎ አልፎ ወደ ፊት ሲሄዱ ለመልሶ ማጥቃት ጥቃት እየተጋለጡ ሀዋሳ ከተማዎች በረጃጅም ኳሶች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ክልል እየደረሱ ጫና ሲያሳድሩ ለመመልከት ችለናል። በአንድ ለአንድ ቅብብል ቀጥለውም በረጃጅም ኳሶች ወደ ተቃራኒ ቡድን ሜዳ ክፍል ሲደርሱ የነበሩት ሀዋሳ ከተማዎች በ34ኛው ደቂቃ መሪነቱን የተረከቡበት ግብ አስቆጥረዋል፤ ፍቃደስላሴ ደሳለኝ በመስመር በኩል በረጅሙ የተጣለውን ኳስ በፍጥነት ደርሶ የስሑል ሽረን ተከላካይ አታሎ በማለፍ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ያሻገረውን ኳስ አሊ ሱሌይማን ወደ ግብ ሲመታት ኳስ ተጨርፎ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።

የአጋማሹ መደበኛ የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ጭማሪ በታየው ላይ በመልሶ ማጥቃት እየገቡ የግብ እድሎችን ሲፈጥሩ የነበሩት ሐይቆቹ ሶስተኛዋን እና መሪነታቸውን ይበልጥ ያጠናከሩበትን ግብ ማግኘት ችለዋል፤ ከራሳቸው ሜዳ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ አሊ ሱሌይማን በግራ መስመር በኩል አግኝቶ ተከላካዩን አታሎ በማለፍ ሳጥን ውስጥ ገብቶ መሬት ለመሬት በመምታት ከመረብ ጋር አገናኝቶ አጋማሹ ላይ አራተኛዋን ግብ ለራሳቸው ደግሞ ሶስተኛውን ግብ አስቆጥሮ የመጀመሪያው አጋማሽ 3ለ1 ተጠናቆ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

ጨዋታው ከእረፍት ሲመልስ ሀዋሳ ከተማዎች ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ አሊ ሱሌይማንን ኢላማ ያደረጉ ኳሶችን ወደ ፊት እያሻገሩ ቀጥለው በ49ኛው ደቂቃ ላይ ያደረጉት ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ይቅር እንጂ ለሀይቆቹ ተጨማሪ ግብ ለመሆን የቀረበ አጋጣሚ ነበር። ስሑል ሽረዎች ከመልበሻ ክፍል መልስ ተጨማሪ ግብ ላለማስተናገድ የተጫዋች ቅያሪዎችን አድርገው ቢመለሱም ግብ ማስተናገዳቸውን መግታት አልቻሉም። በዚህም በ56ኛው ደቂቃ ላይ አራተኛውን ግብ አስተናግደዋል፤ አማኑኤል ጎበና ከተከላካዮች መካአል ያሾለከውን ኳስ አሊ ሱሌይማን አግኝቶ መሬት ለመሬት በመምታት ከመረብ ጋር አጋናኝቶ በጨዋታው ለእራሱ ሶስተኛውን ግብ ለቡድኑ አራተኛውን ግብ አስቆጥሮ 4ለ1 እንዲመሩ አድርጓል።

ስሑል ሽረዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያስችላቸውን ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን ሲያደርጉ ያስተዋልን ሲሆን ፋሲል አስማማው እና ብርሀኑ አዳሙ አልፈው አልፈው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ወደ ግብነች ሳይቀየሩ ይቅሩ እንጂ ተስፋ ሊሰንቃቸው የቀረቡ አጋጠሚዎቸን ፈጥረዋል። ፍፁም የጨዋታ ብልጫ ከግብ ማግባት ጋር የወሰዱት ሐይቆቹ አሊ ሱሌይማን ላይ ትኩረት ባደረጉ አጨዋወት እየተጫወቱ አምስተኛውን ግብ በ68ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥረዋል፤ ከሳጥን ውጪ ሆኖ ኳሱን ያገኘው አሊ ሱሌይማን መሬት ለመሬት ወደ ግብ ጠንከር ያለ ኳስ መጥቶ ከመረብ ጋር ማገናኘት ችሏል።

በርከት ያሉ ግቦች በመቆጠራቸው አኳያ እየተቀዛቀዘ በመጣው በጨዋታው በእንቅስቃሴ ረገድ ሀዋሳ ከተማዎች ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር እድሎችን ሲፈጥሩ ያስተዋልን ሲሆን ስሑል ሽረዎችም በአንፃራዊነት በኳስ ቁጥጥር ጥሩ የተቀንቀሳቀሱ ቢሆንም ጠንካራ የሚባል አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ተቸግረው ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች አምርቷል። 86ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት በቁጥር በርከት ብለው ገብተው ተቀይሮ ሜዳ የገባው ቸርነት አውሽ ኳስ እየገፋ ይዝ ገብቶ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው መልሶበት በድጋሚ አቤነዘር ዩሐንስ ወደ ግብ ያደረገውይ ሙከራ የስሑል ሽረ ተከላካዮች እንዴትም ተረባርበው ያርቁት እንጂ ተጨማሪ ግብ ለመሆን የቀረበ ሌላኛው አጋጣሚ ነበር።

የእለቱ ዋና ዳኛ መስፍን ዳኜ የመጨረሻ ፊሽካቸውን እስኪያሰሙ ድረስ ሐይቆቹ ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ጫና ማሳደራቸውን መቀጠል የቻሉ ሲሆን በግቦች ተንበሽብሸው 5ለ1 በሆነ ውጤት ስሑል ሽረን በማሸነፍ ደረጃቸውን አሻሽለው ጨዋታው ተጠናቋል።

 

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሁለቱም አሰልጣኞች አስተያየት የሰጡ ሲሆን የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ”ዛሬ ከጠበቅነው በላይ አግኝተናል፤ የገቡ ጎሎች አምስት ቢሆኑም ከዛ በላይ እድሎችን አግኝተናል በሁሉም ቦታ ከወትሮው ዛሬ የተሻለ ነው። ብዙ ሰርተን አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ነገር ግን አላለቀም ነገም ሰርተን ወደ ተሻለ ለመሄድ እንጥራለን” የሚል አስተያየት ሲሰጡ የስሑል ሽረ አሰልጣኝ ጌታቸው ደዊት ”የተዘጋጀነው እና ያቅድነውን አሸንፈን ለመውጣት ነበር ይሄንን አልጠበቅንም። ከወገብ በላይ ያለው ቡድናችን ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ነበር፤  ተከላካዮቻችን የአሊን እንቅስቃሴ መቆጣጠር አልቻሉም ያ ነው ዋጋ ያስከፈለን። በተከላካይ ላይ ያደረግነው ቅያሪ ይበልጥ ዋጋ አስከፍሎናል።” የሚል አስተያየት አጋርተዋል።