ሲዳማ ቡና የኢትዮጵያ ዋንጫን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አነሳ

ሲዳማ ቡና የኢትዮጵያ ዋንጫን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አነሳ

ያለ ተመልካች በዝግ የተደረገው የ2017 የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ሲዳማ ቡና 2ለ1 በሆነ ውጤት ወላይታ ድቻን በመርታት ለመጀመሪያ ጊዜ ሻምፒዮን በመሆን በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ይወክላሉ።


በድንገተኛ ውሳኔ ያለ ደጋፊ ለመካሄድ የተገደደው የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ በኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሠማ እየተመራ ጅማሮውን ያደረገ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ማጥቃትን የመረጡት ወላይታ ድቻዎች እንደነበራቸው ብልጫ በ13ኛው ደቂቃ ላይ መሪ ሆነዋል።

ያሬድ ዳርዛ ከሙሉቀን አዲሱ ያገኘውን ኳስ ከቀኝ ወደ ውስጥ ሲያሻማ ሳጥን ውስጥ ራሱን ነፃ አድርጎ የተገኘው ካርሎስ ዳምጠው መረብ ላይ አሳርፏታል ፣ ከጎሏ መቆጠር አንድ ደቂቃዎች በኋላም ከተመሳሳይ የቀኝ የሜዳው ክፍል ሙሉቀን አዲሱ ከቅጣት ምት ያሻገረውን አብነት ደምሴ ሞክሮ የግቡን አግዳሚ ብረትን ኳሷ ለትማ ልትወጣ ችላለች።

ወደ ጨዋታው ለመግባት አስራ አምስት ደቂቃዎችን መሻገር ግድ ያላቸው ሲዳማዎች በፈጣን ሽግግር ለመንቀሳቀስ ጥረት ባደረጉበት ሒደት የአቻነት ግብን አስቆጥረዋል።

20ኛው ደቂቃ ከመስፍን ታፈሠ የተሻገረለትን ኳስ የወላይታ ድቻው የመሐል ተከላካይ መልካሙ ቦጋለ የአቋቋም ስህተት ታክሎ ከጀርባው የተገኘው ሀብታሙ ታደሠ በቀላሉ ጎል አድርጓታል።

ጎሎችን ካስመለከተን በኋላ ይበልጥ መቀዛቀዞች የተበራከቱበት የመጨረሻዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ምንም የተለየ ነገርን ሳያስመለክተን ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ በተመሳሳይ የአንድ አንድ ተጫዋች ቅያሪን በማድረግ የተመለሱት ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን ያደረጉበት ቢሆንም መጠነኛ የአጀማመር ብልጫን የወሰዱት ወላይታ ድቻዎች በ58ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ማስቆጠር ችለው አወዛጋቢ በሆነ የዳኝነት ውሳኔ ተሽሮባቸዋል።

ሙሉቀን አዲሱ ከግራ መስመር በቅጣት ምት ወደ ውስጥ ያሻገረው ኳስ በቀጥታ የቶማስ ኢካራ መረብ ላይ ቢያርፍም ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛው ፋሲካ የኋላሸት ከጨዋታ ውጪ በሚል ሽረውታል።

ከተሻረባቸው ግብ በኋላ በሲዳማ ቡና ብልጫው የተወሰደባቸው የጦና ንቦቹ ከተከታታይ ሙከራዎች በኋላ ጎልን አስተናግደዋል። ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ወደ ጎል አክሮ መቶ የግቡ ቋሚ እና በተከላካይ ተነክታ ወደ ማዕዘን ምትነት የተለወጠች ኳስ ተሻምታ በ62ኛው ደቂቃ መስፍን ታፈሠ ወደ ጎልነት በመለወጥ ሲዳማን ወደ ቀዳሚነት አሻግሯል።


መስፍን ታፈሠ በአንድ ለአንድ ግንኙነት በቢኒያም ገነቱ የተመለሰበት እና ፍቅረየሱስ ከርቀት ካደረጋት ሙከራ በኋላ በመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች በወላይታ ድቻ በብዙ ረገድ የተበለጡት ሲዳማዎች በተለይ ዮናታን ኤልያስ አቻ ሊያደርጋቸው የሚችሉ አራት ያለቀላቸውን አጋጣሚዎች ቢፈጥርም ሳይሳካላቸው በመጨረሻም በሲዳማ ቡና 2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል። የኢትዮጵያ ዋንጫን ለመጀመሪያ ጊዜ በማንሳትም ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያን በአፍሪካ መድረክ መወከሉም ተረጋግጧል።