መቐለ 70 እንደርታ በሊጉ ለመቆየት ኢትዮጵያ ቡና ከዋንጫ ፉክክሩ ለለመውጣት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉበት ጨዋታ 1ለ1 በመጠናቀቁ የቡና ነጥብ መጣል ኢትዮጵያ መድን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን እንዲሆን አስችሎታል።
መቐለ 70 እንደርታ ሲዳማ ቡናን ሲያሸንፉ ይዘው ከገቡት ቋሚ ስብስብ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ብቻ በማድረግ፤ መናፍ አዎልን በቤንጃሚን ኮቴ ተክተው ሲቀርቡ ኢትዮጵያ ቡና በበኩላቸው በአርባምንጭ ከተማ ሽንፈት ከቀመሱበት ቋሚ አሰላለፍ የሶስት ተጫዋች ለውጥ አድርገው፤ ገዛኸኝ ደሳለኝ፣ ሚኪያስ ፀጋዬ እና ዳዊት ሽፈራውን አሳርፈው በምትካቸው ራምኬል ጀምስ፣ አማኑኤል አድማሱ እና ኤርሚያስ ሹምበዛን ይዘው ገብተዋል።
ሁለት በደረጃ ሰንጠረዡ ተቃራኒ ቦታ ላይ የተቀመጡ ቡድኖችን ያገናኘው የረፋዱ ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታን ከ ኢትዮጵያ ቡና ያገናኘ ሲሆን ምዓም አናብስት ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ወሳኝ ጨዋታውን ሲያደርጉ ቡናማዎቹ ከመሪው ጋር ያላቸውን ነጥብ ለማጥበብ ብሎም የዋንጫ ፉክክራቸውን ለማስቀጥል ወደ ሜዳ በመግባታቸው ጠንካራ ፉክክር በጨዋታው ታይቷል።
ቡናማዎቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በወሰዱበት በመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች በአጫጭር ኳስ ቅብብል ከራሳቸው ሜዳ ኳስ መስርተው የተደራጀ እንቅስቃሴ እያደረጉ ወደ ተጋጣሚ ቡድን ሜዳ ክፍል ሲደርሱ ያስተዋልን ቢሆንም በማጥቃቱ ላይ ጥረቶችን ያድርጉ እንጂ እምብዛም ጠንካራ ሙከራ ማድረግ ባይችሉም በ13ኛው ደቂቃ ላይ ዲቫይን ዋቹኩዋ እና አማኑኤል አድማሱ በጥሩ ቅብብል ገብተው ሳጥን ውስጥ ብቻውን ለነበረው ኮንኮኒ ሀፊዝ ኳስ አሻግረውለት መረጋጋት ተስኖት ኳሱን ሳይቆጠጣር የቀረበት ወርቃማው እድል ይታወሳል። ምዓም አናብስት በበኩላቸው ወደ ፊት እየሄዱ አደጋ ለመፍጠር የተቻላቸውን ሁሉ ሲያደርጉ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መመልከት ችለናል፤ 16ኛው ደቂቃ ላይ ኳስ ሳጥን ውስጥ ይዘው ገብተው ተጨራርፎ የወጣውን ኳስ ኢማኑኤል ላርየ ከሳጥን ውጭ ሆኖ ያደረገውን የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ዳንላድ ኢብርሂም አግዶባቸዋል።
ቶሎ ቶሎ ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል በሚደርሱ ሽግግሮች ጋር በታጀበው በጨዋታው ቡድኖቹ ቀዳሚ ለመሆን ፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ አስተውለናል። 28ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከተከላካይ ጀርባ የጣለውን ኳስ ያሬድ ብርሃኑ ደርሶ ከግብ ጠባቂው ፊትለፊት ተገናኝቶ ኳሱን ወደ ግብ አሻግሮ ወደ ውጪ የወጣባቸው አጋጣሚ በአጋማሹ ምዓም አናብስትን መሪ ለማድረግ የቀረበ ወርቃማ እድል ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ሲቀሩ በደቂቃዎች ልዩነት ቡናማዎች ግልፅ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው የነበረ ቢሆንም የምዓም አናብስቱ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው ተረባርበው አውጥተውባቸዋል።
33ኛው ደቂቃ ላይ ቡናማዎች አደገኛ ሙከራ አድርገዋል፤ በተጠቀሰው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ኳስ ይዘው ገብተው አማኑኤል አድማሱ ወደ ግብ የመታው ኳስ ወደ ግብነት ተቀየረ ሲባል ተከላካዩ ሄኖክ አዱኛ እና ኢማኑኤል ላርየ ሲያግዱባቸው እራሱን ኳስ ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ኮንኮኒ ሀፊዝ ወደ ግብ መጥቶ ሶፎንያስ ሰይፌ በግሩም ሁኔታ ኳሱን ከመስመር ያወጣባቸው አደገኛው ሙከራ ቡናማዎችን መሪ ለማድረግ እጅግ በጣም የቀረበ አጋጣሚ ነበር።
ጨዋታው 35ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ምዓም አናብስቶች በያሬድ ከበደ አማካኝነት ያደረጉት ጠንካራ ሙከራ ሲጠቀስ ብሩክ ሙሉጌታ ወደ ሳጥን የጣለውን ኳስ ግብ ጠባቂው ጨርፎ ሲያወጣ ያሬድ ከበደ ጠጠር ኳስ አየር ላይ እንዳለች ወደ ግብ መጥቶ ለጥቂት ከግቡ አግዳሚ በኩል አልፎባቸዋል። በአጋማሹ ሁለቱም ቡድኖች የግብ ማግባት ፍላጎት በብዙ መንገድ ያስመለከቱን እንጂ ጥረቶቹ ጥንካራ ሳይኖራቸው ቀርቶ እምብዛም ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ሳይደርገበት ተገባዶ ወደ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ጨዋታው በሁለተኛ አጋማሽ ተመልሶ 50ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ኢማኑኤል ላርየ ወደ ግብ መትቶ የቡናማዎች ተከላካዮች ያገዱባቸው እንጂ ሁለተኛው አጋማሽ እንደተመለሰ ምዓም አናብስቶች ቀደሚ ለመሆን ቀድሞ ያደረጉት ሙከራ የነበረ ሲሆን በመልሶ ማጥቃት ጥቃት ቡናማዎች ኳስ ይዘው በሚገቡበት ወቅት በሰሩት ጥፋት ቅጣት ምት ለተቃራኒ ቡድን እንዲሰጥ ሆኗል።
52ኛው ደቂቃ ላይ ቡናማዎች ኳስ ወደ ሳጥን ይዘው በሚገቡበት ቅፅበት ሸሪፍ መሐመድ በዲቫይን ዋቹካዋ ላይ በሰራው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ዋሳዋ ጄኦፍሪ ፍፁም ቅጣት ምቱን ወደ ግብ መጥቶ ሶፎንያስ ሰይፈ መመለስ ቢችልም ያገደው ኳስ እራሱ ዋሳዋ ጋር ደርሶ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡናማዎቹን መሪ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
ግብ አስተናግደው ይበልጥ በመነቃቃት ወደ ፊት በመግባት የቡናማዎችን ተከላካይ መስመር እየፈተኑ የቆዩት ምዓም አናብስት ግብ ካስተናግዱ ከአስር ደቂቃ በኋላ የአቻነት ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። 64ኛው ደቂቃ ላይ በመስመር በኩል በጥሩ ቅብብል ገብተው ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አሸናፊ ሐፍቱ ከሄኖክ አዱኛ የተሻገረለትን ኳስ ወደ ሳጥን አሻግሮ ከተከላካዮች ጀርባ ተዘጋጅቶ ሲጠባበቅ የነበረው ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ወደ ግብነት ቀይሮ አቻ አድርጓቸዋል።
የአቻነት ግብ ካስቆጠሩ በኋላ መቐለ 70 እንደርታዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚዎቻቸው ግብ ክልል እየደረሱ የቡናማዎችን ተከላካዮች የፈተኑ ሙከራዎችን ሲያደርጉ መመለክት ብንችልም ሙከራዎቹ ከፈተና የዘለለ አደገኛ እና ለግቡ በደንብ ቀርበው አደገኛ ሳይሆኑ ሲቀሩ አስተውለናል። ቡናማዎች በአንፃራዊነት ወደ ፊት በመሄድ ረገድ የተቀዛቀዛ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን በመልኮ ማጥቃት ግቦችን ለማስቆጠር እየተጣጣሩ ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ድረስ ዘልቋል።
ምዓም አናብስት ከአንድ ነጥብ ይልቅ ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዘው ወጥተው ወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ወደ ፊት በመሄድም ሆነ በሙሉ ሀይላቸው በቁጥር በርከት ብለው ጫና እያሳደሩ በተደጋጋሚ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን በፈጠሩበት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በርከት ያሉ እድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። ሆኖም ግን ወደ ግብነት መቀየር ተስኗቸዋል፤ ይበልጥ ወደግብ የቀረቡበትን ሙከራም 86ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል፤ ሄኖክ አዱኛ የቆመ ኳስ አሻምቶ ቤንጃሚን ኮቴ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ሲታወስ ዳንላድ ኢብራሂምን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ዳዊት ባሕሩ እንዴትም ኳሱን አውጥቶባቸዋል። ጨዋታው ግብ የሚቆጠርበት እየመሰለ ቢቀጥልም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት 1ለ1 በሆነ ውጤት ነጥብ በማጋራት ተቋጭቷል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ ፀጋየ ኪዳነማርያም በፕሪሚየር ሊጉ ላይ ቡድኑን ለመቆየት ተጫዋቾቻቸው ላይ ጫና እንዳለ አንስተው የመጣውን ውጤት በፀጋ ተቀብለው ለቀጣይ ጨዋታ መዘጋጀት እንደሚጠብቃቸው ገልፀዋል። በቀሩት በመቶ ሰማንያ ደቂቃዎች በከፍተኛ ቁርጠኝነት ያላቸውን አቅም አውጥተው ለመጫወት ብዙ እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል። አሰልጣኝ ነፃነት ክብሬ በበኩላቸው በሰጡት አሰተያየት ላለመውረድ የሚያደርጉት ትግል ከባድ እንደሚሆንባቸው አስበው እንደመጡ እና ዛሬ እነሱም ከዚህ በፊት እንደነበረው ልክ እንዳልነበሩ ተናግረው በጎል ቀድመው አቻ የወጡበት የመጀመሪያ ጨዋታ መሆኑን አስታውሰዋል። አሰልጣኙ አክለውም ዋንጫውን ማሳካት ቢችሉ ደስ እንደሚላቸው አንስተው የሚችሉትን ነገር እንዳደረጉ እና ባለማሳካታቸው ደጋፊውን ይቅርታ ጠይቀው ተጫዋቾች ለእስከአሁኑ ጉዞ ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ሁለቱም አሰልጣኞች ለኢትዮጵያ መድን ድርጅት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።