ሪፖርት | ሐይቆቹ በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ ላይ ከፍ ማለታቸውን ቀጥለዋል

ሪፖርት | ሐይቆቹ በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ ላይ ከፍ ማለታቸውን ቀጥለዋል

ሀዋሳ ከተማ በቢኒያም በላይ ብቸኛ ጎል ወልዋሎ ዓ.ዩን 1ለ0 በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል።

ከቀናት በፊት ወልዋሎ ድሬዳዋን 3ለ1 ፣ ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ ስሑል ሽረን 5ለ1 የረታው ቡድናቸው ላይ በተመሳሳይ ምንም ቅያሪን ሳያደርጉ የተገናኙበት ጨዋታ ነበር።

እጅግ ጠንካራ በነበረው የአዳማ ፀሐያማ ዐየር ታጅቦ የጀመረው የሁለተኛ ቀን የሳምንቱ አራተኛ መርሐግብር በመጀመሪያው አጋማሽ በይበልጥ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴዎችን በመበራከታቸው በሙከራዎች በይበልጥ የጎመራ አልነበረም። ከሁለቱ መስመሮች በሚነሱ አልያም ደግሞ ዓሊ ላይ ያተኮሩ ኳሶችን በመጠቀም ማጥቃትን መርጠው የታዩት ሀዋሳዎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ለሰላሳ ያህል ደቂቃዎች ብልጫውን መውሰድ ቢችሉም በ4ኛው ደቂቃ ከቢኒያም በላይ መነሻዋን ያደረገችን ኳስ ብሩክ ታደለ ሳጥን ውስጥ ደርሶት ወደ ጎል ሞክሮ በግቡ አግዳሚ ብረት የተመለሰች ኳስን በድጋሚ አማኑኤል ጎበና ከሳጥን ጠርዝ መቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

ሀዋሳዎች በቅብብል ይሰሯቸው የነበሩ ኳሶችን በማቋረጥ በሽግግር ለመጫወት ጥረት ማድረግን በመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች የተንቀሳቀሱት ቢጫ ለባሾቹ በ30ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል ወደ ቀኝ ናትናኤል ሠለሞን የሰጠውን ኳስ ማጊ አለም ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ፅዮን መርዕድ በጥሩ የቦታ አሸፋፈን ያወጣበት እንዲሁም ሚካኤል ኪዳኔ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ ፂሆን በቀላሉ ከያዘበት ደካማ ሙከራዎች ውጪ በብዙ መልኩ ወረድ ያለ አቀራረቦች የበዙበት የመጀመሪያ አጋማሽ ያለ ጎል ተገባዷል።

ሀዋሳ ከተማ አማኑኤል ጎበናን በአቤኔዘር ዮሐንስ ብሩክ ኤልያስን ደግሞ በቸርነት አውሽ ተክተው የተመለሱበት ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አኳያ የተዳከሙ እንቅስቃሴዎች የበዙበት እና የጠሩ ሙከራዎችንም ለረጅም ደቂቃዎች ያልተመለከትንበት ነበር። ተመጣጣኝ በሚመስሉ አጨዋወት በጎል ሙከራ ግን ኮስታራ መሆን የተሳነው ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ማጊ አለም ለወልዋሎ ከሳጥን ውጪ ያደረጋት ሙከራን ፅዮን መርዕድ ከያዘበት ከሰላሳ ደቂቃዎች በኋላ በትዕግስት ቀስ በቀስ ከጨዋታው አንዳች ነገርን መፈለግ የጀመሩት ሐይቆቹ ግብ አግኝተዋል።

87ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ ቸርነት አውሽ ያስጀመራት ኳስ ሳጥን ውስጥ ወጣቱ ዳንኤል አበራ ለቢኒያም በላይ ሰጥቶት ተፈጥሯዊ ባልሆነው ግራ እግሩ አምበሉ ኳስን መረብ ላይ አሳርፏል። ከጎሏ መቆጠር በኋላ ሀዋሳ ከተማ በአቤኔዘር ዮሐንስ የርቀት ሙከራን ካደረገ በኋላ በብዙ ረገድ ደካማ ፉክክር የነበረው ጨዋታ በሀዋሳ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የወልዋሎው አሰልጣኝ አታክልቲ በርኸ ጨዋታው አሪፍ እንደነበር በመግለፅ ውጤቱ ካደረጉት እንቅስቃሴ አንፃር እንደማይገባቸው እና ውጤቱን ግን በፀጋ ለመቀበል እንደሚገደዱ ጠቁመው ከነበረው ፀሐያማ ዐየር አንፃር መዳከሞች ስለነበሩ ወደ መጨረሻው ደቂቃ ጎል ለማስቆጠር ሊገደዱ ግድ እንዳላቸው ጠቁመዋል። የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ከባድ ጨዋታ እንደነበር በመግለፅ ሜዳ ላይ እንደጠበቁት ተጋጣሚያቸውን እንዳገኙ ከእግዚአብሔር ጋር አሸንፈው መውጣት እንደቻሉ አየሩም ከባድ ከመሆኑ አንፃር በመረጋጋት ውጤት ይዘው እንደወጡ ተናግረዋል።