ጥሩ ፉክክር በታየበት እና 31 የጎል ሙከራዎች በነበሩት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ ስሑል ሽረን 4ለ2 በማሸነፍ በፕሪምየር ሊጉ መክረሙን አረጋግጧል።
ድሬዳዋ ከተማ በ34ኛው ጨዋታ ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ ሲለያዩ ይዘው ከገቡት ቋሚ አሰላለፍ የሶስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ቴዎድሮስ ሀሙ፣ ሄኖክ ሀሰን እና ሀቢብ ከማልን አሳርፈው በምትካቸው አህመድ ረሺድ፣ መስዑድ መሐመድ እና ዘርአይ ገብረስላሴን ይዘው ሲገቡ ስሑል ሽረ ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት በአዳማ ከተማ 4ለ2 ሽንፈት ሲያስተናግዱ ይዘው ከገቡት ቋሚ ስብስብ የአራት ተጫዋች ለውጦች በማድረግ ክፍሎም ገብረህይወት፣ መሐመድ ሱሌይማን፣ ሰለሞን ገብረክርስቶስ እና ሄኖክ ተወልደ አስወጥተው በምትካቸው አሰጋኸኝ ጴጥሮስ፣ ሙሉዓለም መስፍን፣ ጎይቶም ነጋ እና አብዲ ዋበላን በመጀመሪያ ቋሚያቸው ውስጥ አካተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ከሊጉ መውረዳቸውን አስቀድመው ያረጋገጡትን ስሑል ሽረዎችን ለከርሞ በሊጉ ለመቆየት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ከሚገኙት ከድሬዳዋ ከተማዎች ያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ ጨዋታ ብርቱካናማዎቹ ገና በማለዳው ቀዳሚ ለመሆን ወደ ፊት ደርሶ ሙከራዎችን ያደረጉበትን የመጀመሪያ አስር ደቂቃዎች ሲያስመለከተን ጨዋታው ሶስተኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ዘርዓይ ገብረስላሴ ከማዕዘን ምት የተጀመረውን ኳስ እዛው ተቀባብለው ወደ ሳጥን ባሻገረው ኳስ ዮሐንስ ደረጀ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ከግቡ አናት ለጥቂት ይለፍባቸው እንጂ አደገኛው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር።
ወደ ፊት በመሄድ ረገድ ደካማ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነቡሩት ስሑል ሽረዎች ከ15ኛው ደቂቃ በኋላ ተነቃቅተው እጅግ ለግብ የቀረቡ ሁለት ተከታታይ ሙከራዎችን አድርገዋል፣ 15ኛው ደቂቃ ላይ አላዛር ሽመልስ በእራሱ ጥረት ከሳጥን ውጭ ሆኖ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው አላዛር ማረነ ጨርፎ ሲያዋጣባቸው ከሁለት ደቂቃዎች ልዩነት በኋላ በግራ መስመር በኩል ኳስ ይዘው ገብተው ከተከላካይ ጀርባ በተጣለ ኳስ ብርሀኑ አዳሙ ኳስ አግኝቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ከፍ አድርጎ ለማሻገር ሲሞክር ግብ ጠባቂው ጨርፎ ባያወጣባቸው ስሑል ሽረዎች ቀዳሚ ለመሆን እጅግ የተቃረቡበት አስቆጪው ክስተት ይጠቀሳል።
በቁጥር በርከት ብለው የመጀመሪያ ግብ ፍለጋቸውን የቀጠሉት ብርቱካናማዎቹ ከተደጋጋሚ ሙከራዎች በኋላ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። 25ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት መሬት ለመሬት የተጀመረ ኳስ መስዑድ መሐመድ እየገፋ ሳጥን ጠርዝ ይዞ በመግባት ጠንከር ያለ ኳስ ቀጥታ ወደ ግብ መትቶ ከመረብ ጋር ማገናኘት ችሏል።
32ኛው ደቂቃ ላይ ብርቱካናማዎቹ ሌላኛውን ወርቃማ እድል አግኝተዋል፣ በረጅሙ የተጣለ ኳስ አብዱሰላም የሱፍ አግኝቶ ወደ ሳጥን ሲያሻግር ዮሐንስ ደረጀ ወደ ግብ መትቶ ዋልታ አንደይ አግዶበታል። ከሶስት ደቂቃዎች በኋላም እጅግ ያለቀ ኳስ እራሱ ዩሐንስ ደረጀ አግኝቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊትለፊት ተገናኝቶ ወደ ግብ ሲያሻግር ግብ ጠባቂው በጥሩ ቅልጥፍና ኳሱን መልሶባቸዋል። የብርቱካናማዎቹ ጫና በበረታበት በአጋማሹ መገባደጃ አካባቢ ላይ የስሑል ሽረዎቹ ተጫዋች በእራሱ ግብ ላይ ያደረገው ያልተጠበቀ አጋጣሚ ሲጠቀስ 39ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልሰላም የሱፍ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ የስሑል ሽረው ተጫዋች ክብሮም ብርሀነ እንደተቃራኒ ቡድን ሙከራ በእራሱ ግብ ላይ ያደረገው ጠንካራውን ሙከራ ግብ ጠባቂው እንዴትም ያዳነበት አስገራሚው ክስተት በጨዋታው ይታወሳል።
ተጨማሪ ግብ ፍለጋ የተጋጣሚያቸውን ግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ሲጎበኙ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ሁለተኛውን ግብ በአምበላቸው መስዑድ መሐመድ አማካኝነት አስቆጥረዋል። 41ኛው ደቂቃ ላይ ከተከላካይ ጀርባ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ በፍጥነት ደርሶ ተቆጥጥሮ ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ በግሩም ሁኔታ እርጋታ ታክሎበት መሬት ለመሬት መትቶ ኳስና መረብ አገናኝቶ መሪነታቸውን አጠናክሯል።
የአጋማሹ መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ጭማሪ የታየው ላይ ሁለቱም ቡድኖች አደገኛ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን 47ኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ መስዑድ መሐመድ መሬት ለመሬት ከሳጥን ውጭ ለነበረው አቤል አሰበ ኳስ አሻግሮለት ጠጠር ያለ ኳስ ወደ ግብ መትቶ ግብ ጠባቂውና የግቡ አግዳሚ ተጋግዘው ባያወጡባቸው ብርቱካናማዎቹ ሶስት ለባዶ እየመሩ ወደ መልበሻ እንዲገቡ ሊያደርጋቸው የቀረበ የመጨረሻው አደገኛ ሙከራ ሲጠቀስ እራሱን ኳስ በፈጣን ሽግግር በመልሶ ማጥቃት ስሑል ሽረዎች ይዘው ገብተው ብሩክ ሀዱሽ ወደ ግብ የመታውን ኳስ አላዛር ማረን እንዴትም አድኖባቸው አጋማሹ ተገባዶ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።
ጨዋታው በሁለተኛ አጋማሽ ተመልሶ ስሑል ሽረዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ልረዳቸው የቀረበ አጋጣሚ ጨዋታው እንደተመለሰ 47ኛው ደቂቃ ላይ የፈጠሩ ሲሆን በአንድ ለአንድ ቅብብል ገብተው ያደረጉትን ሙከራ አላዛር ማረነ ሶስት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በግሩም ሁኔታ እንዴትም ተረባርቦ አውጥቶባቸዋል። በመጀመሪያዎቹ አምስት ደቂቃዎች የግብ ሙከራዎችን ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታው የተመለሱት ብርቱካናማዎቹ 50ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው ሀቢብ ከማል አማካኝነት ያደረጉት ሙከራ ሲጠቀስ ከማዕዘን ምት የተጀመረውን ኳስ አግኝቶ ሳጥን ውስጥ ይዞ ገብቶ ጠንከር ያለ ኳስ ወደ ግብ መትቶ ለጥቂት ከፍ ብሎ አልፎበታል።
በፈጣን ሽግግር በቀጠለው በጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች በመልሶ ማጥቃት ግቦችን ለማስቆጠር ሙከራዎችን እያደረጉ ቆይተው ጨዋታው 56ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ስሑል ሽረዎች ወደ ጨዋታው መመለስ የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። ሙሉዓለም መስፍን ከተከላካይ ጀርባ የጣለውን ኳስ ብርሃኑ አዳሙ በደረቱ ተቆጣጥሮ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ መረብ ላይ አሳርፎ ወደ ጨዋታ መልሷቸዋል። ሆኖም ግን በአንድ ደቂቃ ልዩነት ብርቱካናማዎቹ ሌላኛውን ግብ አስቆጥረውባቸዋል። 57ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ኳስ ይዘው ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል ደርሰው መስዑድ መሐመድ በግሩም ሁኔታ በተከላካዮች መካከል የሰነጠቀለትን ኳስ ዮሐንስ ደረጀ በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሮ ጨዋታው 3ለ1 እንዲሆን አድርጓል።
በመልሶ ማጥቃት ግለቱን ጨምሮ በፈጣን ሽግግሮች በደመቀው በዚህ ጨዋታ ስሑል ሽረዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የብርቱካናማዎችን ተከላካይ እየፈተኑ በጫና እየተጫወቱ ሲቀጥሉ ብርቱካናማዎቹ በአንፃራዊነት አልፎ አልፎ በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት ሲገቡ ብንመለከትም ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ድክመቶች የታዩባቸውን አጋማሽ እያሳለፉ ጨዋታው ወደ ሰባዎቹ ደቂቃዎች ዘልቋል።
ጨዋታው 75ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ብርቱካናማዎቹ እፎይታ የሰጣቸውን ግብ አስቆጥረዋል፤ አላዛር ማረነ ኳስ ተቆጣጥሮ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ሀቢብ ከማል በፍጥነት ደርሶ ብቻውን ሆኖ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ተከላካዮችን ቀንሶ ኳስና መረብ አገናኝቶ ጨዋታው 4ለ1 እንዲሆን አስችሏል። ምንም እንኳን የግቡ ልዩነት ቢሰፋም ተስፋ ያልቆረጡት ሰሑል ሽረዎች በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ልዩነቱን ያጠበቡትን ግብ አግኝተዋል። ሳጥን ውስጥ በጥሩ ቅብብል ሙሉዓለም መስፍን ያሻገረውን ኳስ አላዛር ሽመልስ ወደ ግብ መትቶ አህመድ ረሺድ ገድቦት እራሱን ኳስ በድጋሚ አግኝቶ ጠንከር ያለ ኳስ ወደ ግብ መጥቶ ዳግም ወደ ጨዋታ እንዲመለሱ ተስፋ የሰነቃቸውን ኳስ አስቆጥሮ ጨዋታው 4ለ2 እንዲሆን አድርጓል።
ብርቱካናማዎቹ ለከርሞ በሊጉ ሊያቆያቸው የሚችል ወሳኝ ሶስት ነጥብ በእጃቸው በማስገባታቸው ምክንያት ጨዋታውን ወደ መጨረስ ገብተው ከወገብ ወረድ ብለው መጫወትን ምርጫቸው ባደረጓቸው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች መከላከሉ ላይ የተጠመዱበትን የጨዋታ መገባደጃ ሲያሳልፉ የተመለከትን ሲሆን በጨዋታው ለግብ የሚሆኑ አጋጣሚዎች ለመፍጠር የተደረገ አስቆጪ እንቅስቃሴ ሳንመለከት ጨዋታውም ለድሬዳዋ ከተማዎች ወሳኝ ሶስት ነጥብ በማስገኘት በ2018 ውድድር ዘመን በሊጉ መቆየታቸውን በማብሰር ተቋጭቷል።
ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ረዳት አሰልጣኝ ተረፈ ሂርጻሳ ጨዋታው ለእነሱ ወሳኝ ከመሆኑን አንፃር ሦስት ነጥብ ለማግኘት መከፈል ያለበትን ነገር ለመክፈል በእያንዳንዱ ቦታዎች ላይ ተነጋገረው እንደገቡ አንስተው ቀጣይ አመት በፕሪሚየር ሊጉ መቆየታቸውን ማረጋገጣቸው ትልቁ እፎይታ እንደሆነ ተናግረዋል። ጊዜያዊ አሰልጣኝ መበራሀቶም ፍስሃ በበኩላቸው በመጀመሪያ አጋማሽ ላይ የትኩረት ማነስ ሁለት ለባዶ እየተመሩ እንዲወጡ እንዳደረጋቸውና በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋች ቅያሪ አድርገው ለመድረስ ቢሞክሩም በመጀመሪያ አጋማሽ የሰሩት ስህተት ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናገረው ቀጣይ አመት ከህዝቡም ከአመራሩም ጋር አንድ ላይ ሆነው በአንድ አመት የክለቡን ክብር አጭር ጊዜ ለመመለስ የተቻለንን ነገር እንሰራለን ብለዋል።