ከሐምሌ 20 ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የሚጀምረው እና በካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ የምስራቅ አፍሪካ ተሳታፊው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አምስት አዳዲስ እና አንድ ነባር ተጫዋቾችን አስፈርሟል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግን ለስምንት ጊዜያት በማንሳት ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የኢትዮጵያ ንግድ ሴቶች ቡድን የተጠናቀቀውን የፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን በበላይነት ማጠናቀቁን ተከትሎ ለተከታታይ አምስተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የቅድመ ማጣሪያ ውድድር ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ። በቀጣዩ ወር መጨረሻ ላይ በሚደረገው በዚህ ውድድር ላይ የሚካፈለው የአሰልጣኝ ብርሀኑ ግዛው ቡድን በመድረኩም ሆነ በ2018 ፕሪምየር ሊግ ራሱን ለማጠናከር አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአንድ ነባርን ኮንትራት ደግሞ ለተጨማሪ አመት ማራዘሙን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ያገኘችው መረጃ አመላክቷል።
ወጣቷ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች እሙሽ ዳንኤል መዳረሻዋ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሆኗል። ከሀዋሳ ከተማ ወጣት ቡድን ከተገኘች በኋላ በተለይ ያለፉትን ሦስት ዓመታት በዋናው የሀዋሳ ቡድን ውስጥ በከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ዝርዝር ውስጥ የነበረችው ተጫዋቿ በእግር ኳስ ህይወቷ ሁለተኛው ክለብ ንግድ ባንክ መሆኑ ታውቋል። በአማካይ ስፍራ ላይ ከይርጋጨፌ ቡና በቀድሞው አጠራሩ ደግሞ ጌዲኦ ዲላ የጀመረው የእግር ኳስ ህይወቷን በመቻል እና ሀዋሳ በማድረግ በሉሲዎቹ ስብስብም እጅግ አስደናቂ ቆይታ የነበራት ባለ ግራ እግሯ እፀገነት ግርማ መዳረሻዋን ሀምራዊ ለባሾቹ ቤት አድርጋለች።
ምርቃት ፈለቀም ሦስተኛዋ የንግድ ባንክ አዲሷ ፈራሚ መሆን ችላለች። ከሻኪሶ ከተማ በአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ዕይታ የክለብ ህይወቷን በሀዋሳ ፣ አዳማ ፣ መቻል ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እንዲሁም ደግሞ የተጠናቀቀውን ዓመት በአርባምንጭ ጀምራ በቂርቆስ ክፍለከተማ የቋጨችው አጥቂዋ ንግድ ባንክን ተመራጭ አድርጋለች። በመስመር እና በአጥቂ ቦታ ላይ ለአቃቂ ቃሊቲ ፣ ይርጋጨፌቡና ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ደግሞ ከሀዋሳ ጋር ያሳለፈችው ሰላማዊት ጎሳዬ ፣ በአርባምንጭ እና መቻል እንዲሁም የተጠናቀቀውን አመት በሀዋሳ ከተማ ያሳለፈችው አማካዩዋ ቤቴልሄም ግዛቸው አዳዲሶቹ የንግድ ባንክ ፈራሚዎች ሆነዋል።
በቡድኑ ውስጥ የነበሩ ተጫዋቾችን በመቀነስ አምስት አዳዲስ ተጫዋቾችን የስብስቡ አካል ያደረገው እና በቀጣዮቹም ቀናት የውጪ ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾች ለማስፈረም በሂደት ላይ የሚገኘው ቡድኑ ለረጅም ዓመታት የቡድኑ ቋሚ ግብ ጠባቂ በመሆን እያገለገለች የምትገኘውን የታሪኳ በርገናን ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት አራዝሟል።
ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ለካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን የማጣሪያ ጨዋታ እና የ2018 የፕሪምየር ሊግ የውድድር ዘመን የሚጠብቀው ንግድ ባንክ ከሳምንት በኋላ ሐምሌ 20 በሀዋሳው ሴንትራል ሆቴል ማረፊያቸውን በማድረግ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የሚጀምሩም ይሆናል።