አንጋፋውን ሙሉጌታ ከበደ ለማሰብ የተቋቋመው ኮሚቴ በይፋ ሥራውን ጀምሯል   

አንጋፋውን ሙሉጌታ ከበደ ለማሰብ የተቋቋመው ኮሚቴ በይፋ ሥራውን ጀምሯል   

“ዝክረ ሙሉጌታ ከበደ” በሚል ስያሜ የተመሰረተው ኮሚቴ በዛሬው ዕለት በይፋ ሥራውን ጀምሯል።

በእግርኳስ ክህሎቱ የደጋፊውን ብቻ ሳይሆን የመላ የእግርኳስ ተመልካቾችን ቀልብ የገዛው እና “ኳስ ታማለች አሉ በጠና በጠና ፤ ሙልዬን ጥሩላት ዶክተሯ ነውና” ተብሎ የተዘመረለት ውልደቱ እና ዕድገቱ ከወሎ የሆነው በቅርቡ ህይወቱ ያለፈው አንጋፋው እና ዝነኛው የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቹ መሉጌታ ከበደ በህይወት እያለ ለሰራቸው ስራዎች እና ላበረከተው አስተዋጽኦ እውቅና በመስጠት ስሙን ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍን አላማ አድርጎ የተቋቋመ ኮሚቴ መሆኑን አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት በቬልቪው ሆቴል በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የቀድሞ የቡድን አጋሮቹ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን ሙሉጌታ ከበደ ያበረከታቸውን አስተዋጽኦዎች በማንሳት በቀጣይ ስሙን የሚመጥን ስራዎችን ለመሥረት የታቀደ ሲሆን በቀጣይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር የሙሉጌታ ከበደን ፋውንዴሽን ለማቋቋም እንዲሁም በስሙ ተቋማትን እና ዘላቂ የሆኑ መታሰቢያዎችን መሰየም፤  ታሪክ እና ገድሉን የሚዘክር ዘጋቢ ፊልም እና መጽሐፍ ማሳተም፤  በሙሉጌታ ስም የተሰየመ አመታዊ አዋርድ ማዘጋጀት እና እንዲሁም በስሙ የስፖርት ማዕከል፣  ሙዚየም እና የእግርኳስ ሜዳዎችን ለመስራት ዕቅድ ተይዟል።

የዝክረ ሙሉጌታ ከበደ ኮሚቴ አባል የሆኑት ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው “እንደ ሙሉጌታ ከበደ አይነት ጀግናዎችን በህይወት እያሉ የሚገባቸውን ክብር መስጠት እና ካለፉም በኋላ ማስታወስ እና ስማቸው እና በጎ ምግባራቸውን ለቀጣይ ትውልድ ማሳለፍ የሁላችንም ድርሻ መሆኑን ተረድተን አስተዋጽኦ እንድናደርግ” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።