👉 “ሥራየን አክብሬ በመሥራቴ እስካሁን ልቆይ ችያለሁ።”
👉 “አዲስ ያስፈረምናቸው የውጪ ተጭዋቾች ላይ መጠነኛ የሆነ ክፍተት ተመልክተንባቸዋል።”
👉 “እግርኳስ ልክ እንደ ደሃ ብርድ ልብስ ነው ምክንያቱም ሁሉንም ባንዴ መሸፈን አትችልም።”
👉 “በፕሮግራም አወጣጡ ላይ ቅሬታ ቢኖረኝም አሸንፈን ለመምጣት የሚገባንን ዝግጅት አድርገናል።”
👉 “ይህንንም ፀጋ እና ጥበብ የሰጠኝ ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን።”
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቻምፒየን በመሆን በኬንያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የካፍ የሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣርያ ውድድራቸውን ሐሙስ ነሐሴ 29 የሚጀምሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ሌሊት ወደ ኬንያ ጉዟቸውን የሚያደርጉ ሲሆን ሶከር ኢትዮጵያም ከቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለተከታታይ አስራ ስድስተኛ አመት ለማሰልጠን በመስማማትህ ምን ተሰማህ?
“ባልተለመደ መልኩ ባለፉት 14 ዓመታት በንግድ ባንክ ቤት ቆይታን ማድረግ ችያለው አሁን ደግሞ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ለመቆየት ውሌን አድሻለሁ። ይህም እንዲሆን ሥራየን አክብሬ በመሥራቴ እስካሁን ልቆይ ችያለሁ ይህንንም ፀጋ እና ጥበብ የሰጠኝ ልዑል እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን። ይህም ለሌሎች ወጣት አሰልጣኞች ትልቅ ትምህርት ይሆናል ብየ አስባለው።”
ስለ ዝግጅት?
“ባለፉት 21 ቀናት በሀዋሳ ዝግጅታችንን ስናደርግ ቆይተናል እዚህም መጥተን ሁለት ሳምንታትን በውድድር አሳልፈናል። በአጠቃላይ 36 ያክል የዝግጅት ቀናቶችን አስቆጥረን ቡድናችንን ለማቀናጀት ሙከራ አድርገናል።”
ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የሴቶች ሲቲ ካፕ ውድድር ቡድናችህን ለመፈተሽ ምን ያክል አግዟችኋል?
“በተጫወትንባቸው ጨዋታዎች ሁሉንም ተጫዋቾች ለማየት ሞክረናል። በአራት ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርብን መውጣት የቻልን ሲሆን በቡድናችን ያለውን የመከላከል እና የማጥቃት ኳሊቲ ለመመልከት ችለናል እናም ይህ ውድድር ክፍተታችንን ለማየት በጣም ረድቶናል። በዚህም አጋጣሚ አዘጋጆችን ከልቤ እያመሰገንኩ ወደ ፊትም ቀጣይነት እንዲኖረው ማለት እወዳለሁ።”
አዲስ ስላስፈረማችኋቸው የዉጭ ተጫዋቾች?
“ያው ትዕግስትን የሚጠይቅ ነገር ነው አሁን ባለው ደረጃ የአየር ንብረቱን ለመላመድ ተቸግረዋል መጠነኛ የሆነ ክፍተትንም ተመልክተንባቸዋል አሁን ሴካፋ ላይ እነሱን ለማየት ሰፊ እድል ይኖረናል።”
ሌሎች አዲስ ፈራሚ ተጫዋቾችስ ከቡድኑ ጋ ተዋህደዋል?
“እግርኳስ ልክ እንደ ደሃ ብርድ ልብስ ነው ምክንያቱም ሁሉንም ባንዴ መሸፈን አትችልም። ያው በሚገባ ተዋህደዋል ብየ ባላስብም እንደ 36 ቀን ጥሩ የሆነ ተግባቦትን መፍጠር ችለዋል።”
ተጋጣሚዎቻችሁን ለማወቅ ምን ያክል ርቀት ሂዳችኋል?
“ከሌሎቹ ዞኖች በተለየ የምድብ ቡድኖችን ቀንሰው እንድንጫወት አድርገውናል። ዉድድሮች ባነሱ ቁጥር የታቀደውን ግብ ለማሳካት አዳጋች ነው የሚሆነው። ያው በውድድሩ ቅሬታ ቢኖረኝም አሸንፈን ለመምጣት የሚገባንን ዝግጅት አድርገናል።”
ዓምና የውድድሩ አሸናፊ ነበራችሁ ፤ ዘንድሮስ ምን እንጠብቅ?
“ባለፉት አራት ዓመታት ዉስጥ በሴካፋ ካደረግናቸው 21 ጨዋታዎች በ16ቱ በማሸነፍ በ3ቱ ተሸንፈን በ አንዱ ብቻ አቻ መውጣት የቻልን ሲሆን ይሄም ለሀገራችን የሴቶች እግርኳስ ትልቅ ስኬት ሲሆን ልክ እንደ አምናው ሁሉ አሸናፊ ለመሆን ዝግጁ ሆነን ወደ ኬንያ ጉዟችንን ለማድረግ ተዘጋጅተናል።”