የኢትዮጵያው ተወካይ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታውን የሚያደርግበት ስታዲየም ዳግመኛ ለውጥ ተደርጎበታል።
ኢትዮጵያን በመወከል በቶታልኢነርጂስ ካፍ ቻምፕዮንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የወቅቱ የሊጉ ቻምፕዮን ኢትዮጵያ መድን በመጀመርያው ዙር ቅድመ ማጣርያ ጨዋታ የዛንዚባሩን ምላንዴግ በድምር ውጤት አራት ለሦስት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉ ይታወሳል።
በቅድመ ማጣርያ የሁለተኛ ዙር ጨዋታ ከግብፁ ፒራሚድ ጋር የሚጫወተው ክለቡ በሜዳው የሚያደርገውን ጨዋታ በአዲስ አበባ ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ለማድረግ መርሐ ግብር ወጥቶለት የነበረ ቢሆንም ካፍ የአበበ ቢቂላ ስታዲየም ካታጎሪ ሁለት ጨዋታዎችን ለማድረግ የሚያስችል መስፈርታ አያሟላም በማለቱ ወደ ሩዋንዳ ተጉዞ ጨዋታውን ለማድረግ ታስቦ እንደነበረ መዘገባችን ይታወቃል።
ሆኖም ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃ ከሆነ ሁለቱም ጨዋታ በግብፅ ካይሮ እንደሚደረግ ታውቋል። ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ መድን የፊታችን አርብ እኩለ ሌሊት ላይ ወደ ስፍራው የሚያቀና ይሆናል።