ፋሲል ከነማ እና ድሬዳዋ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል

ፋሲል ከነማ እና ድሬዳዋ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል

ሐዋሳ ላይ በተደረጉ የዕለቱ ጨዋታዎች ዐፄዎቹ እና ብርቱካናማዎቹ ተጋጣሚያቸውን ማሸነፍ ችለዋል።

ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ፋሲል ከነማ


በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሐዋሳ ምድብ የሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ 9:00 ሲል ወልዋሎ ዓ.ዩን ከ ፋሲል ከነማ አገናኝቷል። ወልዋሎዎች በሲዳማ ቡና 4-1 ከተሸነፉበት ጨዋታ መልስ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እንዲሁም ፋሲል ከነማዎች ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር 1-1 ከተለያዩበት ጨዋታ ማግስት ሶስት ነጥብ ለማሳካት ጨዋታቸውን ጀምረዋል። በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ የሆነ የኳስ ቁጥጥር የነበረበት ቢሆንም 12ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ከርቀት ሞክሮ ግብ ጠባቂው ከመለሰበት ኳስ በስተቀር ይሄ ነው የሚባል ሙከራ ሳያስመለክተን ጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ 52ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል ከነማዎች ከቀኝ መስመር የተሻማውን የቅጣት ምት ግብጠባቂው ቢመልሰውም የተመለሰውን ኳስ ያገኘው በረከት ግዛው ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ድንቅ የሆነ ግብ ማስቆጠር ችሏል። የግቡ መቆጠር መነቃቃት የፈጠረላቸው ዓፄዎቹ 74ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ ያሻማውን ኳስ አቤነዘር ዮሐንስ ግሩም በሆነ መንገድ ግብ አስቆጥሯል። ይህንንም ተከትሎ ዓፄዎቹ ቢጫ ለባሾቹን 2-0 ማሸነፍ ችለዋል።

ወላይታ ድቻ ከ ድሬዳዋ ከተማ


በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሐዋሳ ምድብ የሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታ 12:00 ሲል ወላይታ ድቻን ከ ድሬዳዋ ከተማ አገናኝቷል። ባሳለፍነው ሳምንት ወላይታ ድቻዎች በመቻል 1-0 እንዲሁም ድሬዎች በሀዋሳ ከተማ 2-0 ሽንፈት አስተናግደው ከመመለሳቸው አንፃር ለማሸነፍ የሚያደርጉት ጨዋታ ነው። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ከጅማሮው አንስቶ የሚቆራረጡ ኳሶች የበዙበት ሲሆን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ረገድ ድቻዎች የተሻሉ ቢሆኑም ነገርግን በሁለቱም ቡድን በኩል ዒላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ ሳያስመለክቱ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ 59ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻው ቴዎድሮስ ታፈሰ ያቀበለውን ኳስ መሳይ ሰለሞን ወደ ግብ ቢሞክረውም ለጥቂት በግቡ ቋሚ ጎን ወጥቶበታል። ቅያሪዎችን በማድረግ ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉት ድሬዎች ልፋታቸው ፍሬ አፍርቶ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ 75ኛው ደቂቃ ማስቆጠር ችለዋል። በሜዳው የግራ ክፍል ተቀይሮ ከገባው ሙሀመድኑር ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ያገኘውን ኳስ አብዱልሰላም የሱፍ በጥሩ ዕይታ ያሻማውን ኳስ አቤል ነጋሽ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ይህንንም ተከትሎ ድሬዳዋ ከተማዎች 1-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።