ብርቱካናማዎቹ ጣፋጭ ድል ተቀዳጅተዋል

ብርቱካናማዎቹ ጣፋጭ ድል ተቀዳጅተዋል

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨወታ ድሬዳዋ ከተማ ተቀይረው በገቡ ተጫዋቾች በተገኙ ጎሎች ከመመራት ተነስተው መቐለን 70 እንደርታን አሸንፈዋል።

ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ፍላጎት ያሳዩበት ነበር። በ31ኛው ደቂቃም መቐለ 70 እንደርታዎች ጎል አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ችለዋል። አሰጋኸኝ ጴጥሮስ በጥሩ ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ከደረሰች በኋላ ፍጹም ዓለሙ የሰነጠቃትን ኳስ ተጠቅሞ በድንቅ አጨራረስ መረቡ ላይ ያሳረፋት ግብም ምዓም አናብስትን መሪ ማድረግ ችላለች።

ከዕረፍት መልስ ፈጣን የማጥቃት ሽግግር በማድረግ የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች 49ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ከእጅ ውርወራ የተገኘችውን ኳስ መስዑድ መሐመድ ከቀኝ መስመር ካሻገራት በኋላ መሐመድኑር ናስር በግንባሩ በመግጨት ያስቆጠራት ግብም ብርቱካናማዎቹን አቻ ማድረግ ችላለች። ጎል በተቆጠረባቸው ቅጽበት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የጣሩት መቐለዎች ቦና ዓሊ ወደ ሳጥን አሻግሯት ብርሃኑ አዳሙ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ባመከናት ኳስ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። በድሬዳዋ ከተማዎች በኩልም መሐመድኑር ናስር ከሳጥኑ የግራ ክፍል ሞክሯት ሶፎንያስ ሰይፈ ከመለሰበት ሙከራ በኋላም በተመሳሳይ ሂደት የተገኘችውን ኳስ አቤል ነጋሽ ሞክሮ የግቡ ብረት ጎል ከመሆን አግዶበታል።

በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ በማጥቃት እንቅስቃሴው ብልጫ መወሰድ የቻሉት ምዓም አናብስት 89ኛው ደቂቃ ላይ መሪ ሊሆኑ የሚችሉበትን እጅግ ያለቀለት የግብ ዕድል በአሸናፊ ሐፍቱ አማካኝነት ማግኘት ቢችሉም ሙከራዋ በፍሬው ጌታሁን ጥሩ ቅልጥፍና ተመልሳለች። ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ አራት ደቂቃዎች ውስጥም ብርቱካናማዎቹ ጣፋጭ ድል ያሳኩበትን ጎል አግኝተዋል። አብዱልሰለም የሱፍ በግሩም ሁኔታ እየገፋ የወሰደውን ኳስ ለመስዑድ አቃብሎት ከደቂቃዎች በፊት ትልቅ ዕድል አባክኖ የነበረው አማካዩ ወደ ሳጥን ያሻገረው ኳስ ሲመለስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው አቤል አሰበ በድንቅ አጨራረስ ኳሱን ከመረብ ላይ አሳርፎታል።