በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የምድብ 2 የ9ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ነገሌ አርሲዎች ወደ አሸናፊነት ሲመለሱ አዞዎቹ እና ቡናማዎቹ ያለ ግብ ተለያይተዋል።
ሀድያ ሆሳዕና ከ ነገሌ አርሲ
ሀድያ ሆሳዕና ከ ነጌሌ አርሲ ባገናኘው ጨዋታ በጅማሮው በግብ የታጀበ ሁነትን ያስመለከተን ሲሆን 5ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ሂደት ግብ ጠባቂው ኢድሪሱ አብዱላሂ በድንቅ ዕይታ ከተከላካይ ጀርባ ያሻገራትን ኳስ ከቤ ብዙነህ ከግብ ጠባቂው ኦውሱ እንድሪውስ ጋር ተሻምቶ ከሳጥን ውጭ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኋላ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት ሀድያ ሆሳዕናዎች 23ኛው ደቂቃ ላይ እዮብ አለማዮህ ከብሩክ በየነ የተቀበላትን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ነብሮቹን አቻ ማድረግ ችሏል፡፡

ከዕረፍት መልስ ተመጣጣኝ የኳስ እንቅስቃሴ የታየበት ቢሆንም ግብ በማስቆጠር ረገድ ቀዳሚ የነበሩት ግን ነገሌ አርሲዎች ነበሩ፡፡ 68 ኛው ደቂቃ ላይ ከቤ ብዙነህ እንደ መጀመርያው ግብ በመልሶ ማጥቃት ሂደት ያገኘውን ኳስ ከሳጥኑ ጠርዝ መቶ በማስቆጠር ለራሱና ለቡድኑ ሁለተኛ ግቡን አስቆጥሯል፡፡ ከግቧ መቆጠር በኋላ የሁለት ግቦች ባለቤቱ ከቤ ብዙነህ ከቆመ ኳስ ድንቅ ሙከራ ማድረግ ቢችልም በግብ ጠባቂው ጥሩ ብቃት ግብ ከመሆን ተርፏል፤ ጨዋታውም ነገሌ አርሲዎች በከቤ ብዙነህ ሁለት ግቦች ታግዘው 2-1 በሆነ ውጤት ሀድያ ሆሳዕናን አሸንፈዋል፡፡

አርባ ምንጭ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
በሙከራዎች ረገድ የተቀዛቀዘ በነበረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ከራሳቸው የግብ ክልል ኳስን መስርተው በመጫወት በተደጋጋሚ የተጋጣሚያን የግብ ክልል መጎብኘት ቢችሉም
29ኛው ደቂቃ ላይ ሚኪያስ በዳሶ ከፍቃዱ አለማየሁ የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ከሞከረው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጭ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። አርባምንጭ ከተማዎች በበኩላቸው መከላከልን ምርጫቸው በማድረግ በቁጥር በዛ ብለው በማፈግፈግ የመጀመሪያውን አጋማሽ ግብ ሳያስተናግዱ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ እምብዛም የግብ ሙከራ ያላስመለከተን ነበር፡፡ የአጋማሹ የጨዋታ ሂደት በብዛት በመሀል ሜዳ ዙሪያ የተካሄደ ሲሆን በኳስ ቁጥጥር እና በማጥቃት እንቅስቃሴ ረገድም ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻሉ ነበሩ፤ ሆኖም የአርባምንጭ ከተማዎች ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት አልፈው በርከት ያሉ የጠሩ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ማለትም በ87ኛው ደቂቃ ላይ ግን በፍቃዱ አለማየሁ እና አቡበከር አዳሙ ድንቅ በሆነ የአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ግብ ክልል ይዘውት የገቡትን ኳስ በፍቃዱ አለማየሁ ወደ ግብነት ለመቀየር ያደረገው ሙከራ ለጥቂት በግቡ ቋሚ ወጥቶበታል፡፡ በሙከራዎች ያልታጀበው የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታም ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል።


