በአዳማ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ እና ባህርዳር ከተማ ያለ ግብ ሲለያዩ መቐለ 70 እንደርታ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2ለ1 በማሸነፍ ወሳኝ ድል አስመዝግቧል።
ወላይታ ድቻ ከ ባህርዳር ከተማ
የ16ኛው ሳምንት መከፈቻ የነበረው የጦና ንቦቹ እና የጣና ሞገዶቹ ያፋለመው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥቂት የግብ ሙከራዎች እና ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። የጦና ንቦች በአጋማሹ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ ቢችሉም ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ዮናታን ኤልያስ ካደረጓቸው ግብ ጠባቂውን ያልፈተኑ ሙከራዎች ውጭ ይህ ነው የሚባል ወደ ግብነት የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። የጦና ንቦቹን ተከላካይ መስመር የፈተነ እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻሉት የጣና ሞገዶቹም በአጋማሹ ለግብ የቀረበ ሙከራ አላደረጉም።

ሁለተኛው አጋማሽ የጦና ንቦቹ በኳስ ቁጥጥር እና ጫናዎችን በመፍጠር የነበራቸውን ብልጫ ያጠናከሩበት ነበር። በአጋማሹ ተሻሽሎ የቀረበው ቡድኑ የተሻለ ጫና በፈጠረባቸው ደቂቃዎችም ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችሏል። ያሬድ ዳርዛ ከሳጥኑ ጠርዝ መሬት ለመሬት መቶት ፔፔ ሰይዶ የተቆጣጠረው ሙከራም የአጋማሹ ቀዳሚ ሙከራ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪ ያሬድ ዳርዛ በግሩም ሁኔታ እየገፋ በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ቀንሶለት ያንኑ ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው ቴዎድሮስ ታፈሰ በችኮላ የመታው እና በግቡ አግዳሚ በኩል የወጣው መከራም በጨዋታው የተሻለው የግብ አጋጣሚ ነበር። አልፎ አልፎም ቢሆን ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ለመድረስ ጥረት ያደርጉት የጣና ሞገዶች ግን በአጋማሹ አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።
እስከ ጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ድረስ ጫና መፍጠራቸውን የቀጠሉት ወላይታ ድቻዎች ከተጠቀሱት ሙከራዎች በተጨማሪ ካርሎስ ዳምጠው ከመአዝን የተሻገረችውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባሩ ባደረጋት ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው ፍሬ ሳያፈራ ቀርቶ ብዙም ሳቢ ያልነበረው እና 27 ጥፋቶች የተስተናገዱበት ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም የጦና ንቦች ስምንተኛ አቻ ውጤት ሲያስመዘገቡ የጣና ሞገዶች ዘጠናኛ አቻ ውጤት አስመዝግበዋል።
መቐለ 70 እንደርታ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ታጅቦ የጀመረው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የመቐለ 70 እንደርታዎች ሙሉ ብልጫ የታየበት ነበር። ፈጣን አጀማመር የነበራቸው ምዓም አናብስቶቹ በ10ኛው ደቂቃ ላይም በጊት ጋት ኮች አማካኝነት ጨዋታውን መምራት የቻሉበት ግብ አስቆጥረዋል። ቁመታሙ ተጫዋች የመስመር ተከላካዩ ደስታ ዩሐንስ ከቆመ ኳስ አክርሮ መቷት ግብ ጠባቂው ያልተቆጣጠራትን ኳስ አግኝቶ ከመረቡ ጋር በማዋሀድ ነበር ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለው።
ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በአጋማሹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ቢችሉም የምዓም አናብስቱ የተከላካይ መስመር አልፈው ዕድሎችን መፍጠር አልቻሉም። መቐለ 70 እንደርታዎች ግን በረዣዥም ኳሶች እና በፈጣን ሽግግሮች ጫና መፍጠራቸው ሲቀጥሉ ፍፁም ዓለሙ በጥሩ መንገድ ወደ ሳጥን ይዟት የገባውን ኳስ መትቶ ግብ ጠባቂው ከተቆጣጣራት ሙከራ በኋላም በ29ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ፍፁም ዓለሙ የቀኝ መስመር ተከላካዩ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ በረዥሙ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ሳጥን ይዞ በመግባት መሬት መሬት መቶ ያስቆጥራት ግብም የምዓም አናብስቱን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች።

ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር የተደረበት እና ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የተሻለ ጫና የፈጠሩበት ነበር። በረጃጅም ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ኤሌክትሪኮች አጋማሹ በተጀመረ በ5ኛው ደቂቃ ላይም ወደ ጨዋታው የመለሰቻቸው ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ሀብታሙ ሸዋለም ከማዕዘን አሻግሯት በመቐለ 70 እንደርታ ተጫዋቾች የመናበብ ችግር በቀጥታ ከማዕዘን ምት ወደ ግብነት የተቀየረችው ኳስም ኤሌክትሪኮችን ተስፋ ያሰነቀች ግብ ነበረች።
ቀጥለው የነበሩ ደቂቃዎች ኤሌክትሪኮች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ጫና ፈጥረው የአቻነት ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉበት ምዓም አናብስቱ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ ለማግኘት የተንቀሳቀሱት ቢሆንም የኤሌክትሪኩ ሀብታሙ ሸዋለም ከሳጥን ውጪ ካደረገው ሙከራ ውጭ በሁለቱም በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ሳይደረግ በምዓም አናብስቶቹ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል።

