ሪፖርት| ሰጎኖቹ ድል ሲያደርጉ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ባህርዳር ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት| ሰጎኖቹ ድል ሲያደርጉ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ባህርዳር ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከሁለት ለባዶ መመራት ተነስተው ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋሩ ነገሌ አርሲዎች ወሳኝ ድል አሳክተዋል

ባህር ዳር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የጣና ሞገዶቹ ከ ሀምራዊ ለባሾቹ ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያዎችን አስር ያክል ደቂቃዎች ንግድ ባንኮች የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን 11ኛው ደቂቃ ላይ ሳይመን ፒተር ከሁዘይፋ ሻፊ ተቀብሎ በሞከረው እና ፔፔ ሳይዶ ባወጣበት ሙከራም የመጀመሪያው የግብ ዕድል መፍጠር ችለዋል። ነገር ግን ቀሪዎቹን የአጋማሹ ደቂቃዎች ባህር ዳር ከተማዎች ብልጫ የወሰዱበት ነበር። 28ኛው ደቂቃ ላይ ወንድወሰን በለጠ ከብሩክ ሰሙ እንዲሁም 44ኛው ደቂቃ ላይ ዮሐንስ ደረጀ ከ አናንያ ጌታቸው የተቀበሏቸውን ኳሶች ሳጥን ውስጥ ሆነው ወደ ግብ ሞክረውት በግብ ጠባቂው አማኑኤል ደስታ ጥሩ ቅልጥፍና የተመለሱ ኳሶችም በጣና ሞገዶቹ በኩል የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው።

አራት ግቦችን ባስመለከተን ሁለተኛው አጋማሽ 57ኛው ደቂቃ ላይ ባህር ዳር ከተማዎች የመጀመሪያ ግባቸውን አስቆጥረዋል። ግርማ ዲሳሳ ከሜዳው የግራ መስመር ይዞ ገብቶ የግብ ዕድል ለመፍጠር በሚመስል መልኩ ያሻገረው ኳስ በግብ ጠባቂው አማኑኤል ደስታ እግር ሸልኮ ከመረብ ጋር በመዋሀድ የጣና ሞገዶችን ቀዳሚ አድርጓል። ከግቡ መቆጠር በኋላም ተጨማሪ ግቦችን ለማግኘት ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ባህር ዳር ከተማዎች 67ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን ከፍ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችለዋል፤ ብሩክ ሰሙ በድንቅ ዕይታ አመቻችቷት ወንድወሰን በለጠ በጥሩ ሩጫ ግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም የቡድኑን መሪነቱን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችላለች።

ሆኖም ከአንድ ደቂቃ በኋላ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች የግብ ልዩነቱን ወደ አንድ ዝቅ ማድረግ ችለዋል። 68ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ዋሼ መራት ለመራት ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ወጣቱ ሁዜይፋ ሻፊ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም ሀምራዊ ለባሾቹን ወደ ጨዋታው መልሳለች። በቀሩት ደቂቃዎች የአቻነት ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው የተንቀሳቀሱት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በ80ኛው ደቂቃ ላይ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ሳይመን ፒተር በግንባሩ ባስቆጠራት ግብ አቻ መሆን ችለዋል። በሁለተኛው አጋማሽ አራት ግቦች የተቆጠሩበት ጨዋታም 2 – 2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

 

ነገሌ አርሲ ከ መቐለ 70 እንደርታ

 

ነገሌ አርሲን ከ መቐለ 70 እንደርታ ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ነገሌ አርሲዎች መጠነኛ ብልጫ የወሰዱበት እንዲሁም በሙከራዎች ያታጀበ ነበር። አጋማሹ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይሄ ነው የሚባል የግብ ሙከራን ሳያስመለክተን ረዘም ላሉ ደቂቃዎች ከዘለቀ በኋላም በ41ኛው ደቂቃ ላይ ሮኅቦት ሰላሎ ከርቀት ባስቆጠራት ድንቅ የቅጣት ምት ግብ ሰጎኖቹን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ መቐለ 70 እንደርታዎች ጥሩ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን 56ኛው ደቂቃ ላይ ጊትጋት ኮች ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ባደረገው እና ለጥቂት በአግዳሚው በወጣው እንዲሁም ቦና ዓሊ ከሳጥን ውጭ መቶት ግብ ጠባቂው በያዘበት ሙከራ ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር። በሰጎኖቹ በኩልም ሮኅቦት ሰላሎ በድጋሚ ከቅጣት ምት መሬት ለመሬት አክርሮ የመታው እና በግብ ጠባቂው የተመለሰው ሙከራ ይጠቀሳል። 83ኛው ደቂቃ ላይም የመቐለ 70 እንደርታው ተጫዋች ጊት ጋትኮች ገብረመስቀል ዱባለ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የዕለቱ ዋና ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ አሰናብተውታል።

ብዙም በሙከራዎች ባልታጀበው ጨዋታም ሰጎኖቹ በሮኅቦት ሰላሎ ግሩም የቅጣት ምት ግብ አማካኝነት 1-0 ማሸነፍ ችለዋል።