ሪፖርት | ንግድ ባንክ ወደ አሸናፊነት ሲመለስ ምድረ ገነት ሽረ እና ፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ንግድ ባንክ ወደ አሸናፊነት ሲመለስ ምድረ ገነት ሽረ እና ፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋርተዋል

ዛሬም በቀጠለው በ23ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የአዳማ ጨዋታዎች ንግድ ባንክ 2ለ1 በሆነ ውጤት ድሬዳዋ ከተማን ሲረታ ምድረ ገነት ሽረ እና ፋሲል ከነማ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

ምድረ ገነት ሽረ ከ ፋሲል ከነማ

በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ ፉክክር ቢታይበትም በኳስ ቁጥጥሩ አፄዎቹ ከምድረ ገነት ሽረ የተሻሉ ሆነው ታይተውበታል። ይሄም ቢሆን በሁለቱም በኩል  አንድም ለጎል የቀረበ ሙከራ መመልከት ያልቻልንበት አጋማሽ ሆኖ አልፏል።

ከዕረፍት መልስ ተነቃቅተው የመጡት ፋሲል ከነማዎች በግሩም የቡድን ስራ የጨዋታውን የመጀመርያ ጎላቸውን አስቆጥረዋል። 56ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ዳግም አወቀ የተነሳውን ኳስ በጥሩ መንገድ ለበረከት የሰነጠቀለትን በረከት ግዛው ለታምራት አቀብሎት በተረከዝ የመለሰለትን በረከት ግዛው በድንቅ አጨራረስ ኳሱን መረቡ ላይ አስቀምጦታል።

ፋሲሎች ከጎሉ በኋላ ወደ ራሳቸው ሜዳ አፈግፍገው ቢከላከሉም በመልሶ ማጥቃት ሁለተኛ ጎል ለመስቆጠር ተቃርበው ነበር። በ83 ኛው ደቂቃ ቃልኪዳን ዘላለም ጥሩ የጎል አጋጣሚ ቢፈጥርም የግቡ ግራ ቋሚ ከልክሏቸዋል።

የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ የአቻ ነት ጎል ፍለጋ የታተሩት ምድረ ገነት ሽረዎች 89ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ተክለ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ዳንኤል ግርማይ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን አቻ አድርጓል። ጨዋታውም አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በማስከተል በተካሄደው የድሬዳዋ ከተማ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የምሽቱ ጨዋታ በፍጥነት ነበር ጎል መቆጠር የጀመረው። 14ኛው ደቂቃ የድሬዋው ግብ ጠባቂ አብዮ ካሳሁን ኳሱን ከራሱ ሜዳ ለማስጀመር የሰራውን ስህተት አዲስ ግደይ ኳሱን አግኝቶ ቺፕ በማድረግ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ድሬዳዋ ከተማዎች 54ኛው ደቂቃ አብዲሳ ጀማል ከርቀት አክርሮ የመታውን የግቡ አግዳሚ የመለሰበት የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በሁሉም የሜዳ ክፍል ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት ድሬዎች 61ኛው ደቂቃ ላይ የንግድ ባንክ ተከላካዮች ከራሳቸው ሜዳ ማራቅ ያልቻሉትን ኳስ በመሐመድኑር ናስር አግኝቶ በግንባሩ ገጭቶ ቡድኑን አቻ አድርጓል።


ምላሽ ለመስጠት ያልዘገዮት ንግድ ባንኮች በ67ኛው ደቂቃ  አዲስ ግደይ በጥሩ መንገድ የያቀበለውን ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ዳንኤል በግንባሩ መቶ ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር ቡድኑን በድጋሚ መሪ ማድግ ችሏል።

በድጋሚ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የፈለጉት ድሬዳዋ ከተማዎች 73ኛው ደቂቃ በአቤል ነጋሽ አማካኝነት አቻ የሚሆኑበት አጋጣሚ ቢፈጥሩም ግብጠባቂው ጆርጅ ደስታ ከልክሏቸዋል። ጨዋታውም በንግድ ባንክ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።