ሊጉ በብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ከመቋረጡ በፊት የሚካሄዱ የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች።

መቐለ 70 እንደርታ ከ ወላይታ ድቻ
በሀያ ሁለት ነጥብ 19ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ከገጠማቸው ሁለት ተከታታይ ሽንፈት ለማገገምና ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እየተደረገ በሚገኘው ፍልሚያ ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ያደርጋሉ። በመጀመሪያዎቹ የሁለተኛው ዙር ጨዋታዎች ሽረ ምድረ ገነትን አሸንፈው ከመቻል ጋር ነጥብ በመጋራት በወራጅ ቀጠናው መውጫ በር የነበሩት መቐለ 70 እንደርታዎች በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በተከታታይ ሽንፈት ማስተናገዳቸውን ተከትሎ ደረጃቸው እንዲያሽቆለቁል ሆኗል። በ3ኛው እና 4ኛው ሳምንት ላይ በድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ከገጠመው ተከታታይ ሽንፈት በኋላ በመደዳ ሽንፈት ሳይቀምስ ለ19 ሳምንታት ዘልቆ በድጋሚ በድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ተከታታይ ሽንፈት የገጠመው ቡድኑ በአራት ነጥቦች ከፍ ብሎ ከተቀመጠው የቅርብ ተፎካካሪው በሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ ላይ አባካኝነቱን መቅረፍ ያልቻለውን የፊት መስመሩን አፈፃፀም ማሻሻል እንዲሁም በቅርብ ሳምንታት ድክመቶች እየተስተዋለበት የሚገኘውን የተከላካይ ክፍሉ ማስተካከል ይኖርበታል።
ሀያ ስድስት ነጥቦች ሰብስበው 17ኛ ደረጃ ላይ ያሉት ወላይታ ድቻዎች ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ እያደረጉት ያለው ግሩም ጉዞ ለማሳለጥ በአራት ነጥብ ዝቅ ብሎ ከተቀመጠው መቐለ 70 እንደርታ ጋር ይፋለማሉ። የጦና ንቦቹ በመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ መርሐ ግብር በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ካስተናገዱ ወዲህ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ከወራጅ ቀጠናው መውጣት የቻሉበት ድንቅ ጉዞ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች ሦስት ድል እና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥብ አስሩን በማሳካት አስደናቂ ግስጋሴ በማድረግ ላይ የሚገኘው ቡድኑ ውጤቶቹን ተከትሎ ከነበረበት ወራጅ ቀጠና መውጣት ችሏል። የጦና ንቦቹ የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና፤ ተከታዩ ሀዋሳ ከተማ፤ ከመሪዎቹ ጎራ ያለው መቻል እና ድሬዳዋ ከተማ በገጠሙባቸው መርሐ ግብሮች ሦስት ድሎች ማስመዝገባቸው እንዲሁም በጨዋታዎቹ 10 ግቦች ማስቆጠራቸውም ያሉበትን ድንቅ ወቅታዊ ብቃት ማሳያ ነው። በቅርብ ሳምንታት ያሳዩትን ውጤታማ እንቅስቃሴም ማስቀጠልም የቡድኑ ቀዳሚ ስራ ነው።
መቐለ 70 እንደርታዎች ፍሬዘር ካሳን በቅጣት ብሩክ ቃልቦሬን ደግሞ በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም። በወላይታ ድቻ በኩል ግን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ቡድኖቹ በሊጉ ለሰባት ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን ሁለቱም በእኩሌታ ሦስት ሦስት ጨዋታዎቹን ድል ሲያደርጉ በተቀረው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል፤ መቐለ 6 ሲያስቆጥር ድቻ 5 ግቦችን አስቆጥሯል።
ነጌሌ አርሲ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
በሰላሣ ስምንት ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ነጌሌ አርሲዎች ድል አድርገው ሁለተኛ ደረጃነት ለመቆናጠጥ በአራት ነጥቦች ዝቅ ብሎ ከተቀመጠው ኤሌክትሪክ ጋር ይፋለማሉ።
በመጨረሻው ጨዋታ ከባህርዳር ከተማ ጋር አቻ የተለያዩት እና በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻሉት ሰጎኖቹ በቅርብ ሳምንታት ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ወደ ሊጉ አናት ይበልጥ እንዳይጠጉ አድርጓቸዋል። ሦስት ተከታታይ ድሎች ካስመዘገበ በኋላ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ዘጠኝ ነጥብ ጥሎ ሦስቱን ብቻ ያሳካው ቡድኑ ዳግም ወደ ቀደም ብቃቱ ለመመለስም ባለፉት አራት መርሐ ግብሮች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረውና ኳስና መረብ ካገናኘ ሦስት ጨዋታዎች ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወቱ ማሻሻል ይጠበቅበታል።
ሰላሣ አራት ነጥቦች ሰብስቦ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለት ደረጃዎችን አሻሽሎ 4ኛ ደረጃ ላይ የሚያስቀምጠውን ድል ለማግኘት ይፋለማል። ሦስት ሽንፈቶች እና ሦስት የአቻ ውጤቶች ካስመዘገቡባቸው ስድስት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ተከታታይ ሁለት ድሎች ያስመዘገቡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ባለፉት ሁለት መርሐ ግብሮች በሁሉም ረገድ የተሻሻለ ብቃት በማሳየት ዳግም ወደ ጥሩ ብቃት ተመልሰዋል። በተለይም በአምስት መርሐ ግብሮች ኳስና መረብ ሳያገናኝ ከዘለቀ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ያስቆጠረው የፊት መስመር በቡድኑ ውጤት ማማር የአምበሳውን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል። ቋሚ ተሰላፊዎቻቸው በፍቃዱ አስረሳኸኝ፣ በረከት ወልደዮሐንስ እና አሸናፊ ጥሩነህን በማያሰልፉበት የዛሬው ጨዋታም በቅጣት ምክንያት ወሳኝ ተጫዋቾችን ያጣው የኋላ ክፍሉ ማጠናከር እንዲሁም የፊት መስመራቸውን ውጤታማ አካሄድ ማስቀጠል ይኖርባቸዋል።
ነጌሌ አርሲዎች ሀቢብ ከማልን በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል አሸናፊ ጥሩነህ ፣ በረከት ወልደዮሐንስ እና በፍቃዱ አስረሳኸኝ በቅጣት ምክንያት አይኖሩም።
ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረጉት ጨዋታ 0 ለ 0 መጠናቀቁ ይታወሳል።

