ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሀሰን ሁሴን ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች ነገሌ አርሲን በማሸነፍ የሀዋሳ ቆይታቸውን በድል አጠናቀዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ከፍተኛ ብልጫ በወሰዱበት በመጀመሪያው አጋማሽ 20ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ሀብታሙ በጥሩ እይታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ሀሰን ሁሴን ጥሩ በሆነ በራስ መተማመን ግብ ጠባቂውን አታሎ በማለፍ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል።

29ኛው ደቂቃ ላይ የነገሌ አርሲ ተጫዋች የሆነው ግዙፉ ተከላካይ ዲሴሬ ፓስካል ኤሌክትሪኮች የፈጠሩትን ግልጽ የሆነ የግብ ማግባት እድል ኳስን በእጁ ነክቶ በማቋረጡ የተነሳ በዕለቱ ዋና ዳኛ ሃይማኖት አዳነ አማካኝነት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
የቁጥር ብልጫውን እንደ መልካም አጋጣሚ የተጠቀሙት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች 37ኛው ደቂቃ ላይ አንዋር በድሩ ያቀበለውን ኳስ በአጋማሹ በጥሩ ሁኔታ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሀሰን ሁሴን ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ አክርሮ በመምታት ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሯል።

ቀዝቀዝ ባለ ዝናባማ አየር የተጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ነገሌ አርሲዎች 48ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ተፈራ ከቅጣት ምት ሞክሮት ግብ ጠባቂው ባዳነበት እንዲሁም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች 72ኛው እና 73ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ሀብታሙ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ ባበከናቸው እንዲሁም የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ተቀይረው በገቡት አብዱልመጂድ ሁሴን እና አብነት ተስፋየ ሙከራዎች ተጨማሪ ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ነገር ግን ሌሎች ግቦችን ሳያስመለክተን ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

