መቐለ 70 እንደርታ እና ወላይታ ድቻን ያፋለመው ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ።

ምዓም አናብስት እና የጦና ንቦች ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ቢሆንም በሙከራዎች የታጀበ አልነበረም። በጨዋታው ጅማሮ ብልጫ የነበራቸው እና ጫና ፈጥረው ሙከራዎች በማድረግ ቀዳሚ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ሲሆኑ ያሬድ ዳርዛ ከሳጥኑ ጠርዝ መቶት ሶፎንያስ ሰይፈ ያዳነው፤ ኪዳኔ አሰፋ ከሳጥን ውስጥ ሆኖ መቷት አብዲ ዋበላ ተደርቦ ያወጣት እንዲሁም በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ያሬድ ዳርዛ ከግቡ ቅርብ ርቀት ሆኖ ያመከነው አጋጣሚም በጦና ንቦቹ በኩል የተደረጉ ሙከራዎች ናቸው። በሂደት የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመሩት መቐለ 70 እንደርታዎችም ቦና ዓሊ ከአሸናፊ ሀፍቱ የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ባደረጋት እና ብርሀኑ አዳሙ ከሳጥኑ ውጭ አክርሮ መቶት የግቡ ቋሚ በመለሰበት ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል።

እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የተቀዛቀዘ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተደረገበት ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ ቡድኖች በርከት ያሉ ጥራት ያላቸው ዕድሎች ያልፈጠሩበት ነበር። በመቐለ 70 እንደርታ በኩል አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል አክርሮ መቶት ካዲም ንዳዬ ያዳነው እና አሸናፊ ሀፍቶ ሳጥን ውስጥ ከፍ አድርጎ ለማስቆጠር መቷት ግብ ጠባቂው በግሩም መንገድ ያዳናት አጋጣሚዎች ሲጠቀሱ በወላይታ ድቻ በኩል ደግሞ ያሬድ ዳርዛ ከመቐለ ተከላካዮች አምልጦ ያደረገውና ሶፋንያስ ሰይፈ በጥሩ ብቃት ወጥቶ ያዳነው እንዲሁም ዮናታን ኤልያስ ከቆመ ኳስ በቀጥታ መቶት የግቡን አግዳሚ የመለሰው ወርቃማ አጋጣሚ ተጠቃሽ ሙከራዎች ናቸው። ቡድኖቹ በታሪካቸው ለስምንተኛ ጊዜ ያደረጉት ጨወታም ግብ ሳይቆጠርበት ባዶ ለባዶ ተጠናቋል።

