ሪፖርት| የጣና ሞገዶቹ ወደ ድል ተመልሰዋል

ሪፖርት| የጣና ሞገዶቹ ወደ ድል ተመልሰዋል

ባህርዳር ከተማ በብሩክ ሰሙ እና አንተነህ ተፈራ ግቦች አዳማ ከተማን 2ለ1 ረቷል

9፡00 ሲል በዋና ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ ጥሩ አጀማመር ያደረጉት የጣና ሞገዶቹ 18ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። መሳይ አገኘሁ ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ብሩክ ሰሙ በግንባሩ በመግጨት መረብ ላይ አሳርፎታል። ባህር ዳሮች ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም በጥሩ ቅብብል ተጨማሪ የግብ ዕድል ፈጥረው በስተመጨረሻም ወንድወሰን በለጠ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ናትናኤል ተፈራ በጥሩ ቅልጥፍና አግዶበታል። ጨዋታው 26ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስም ግርማ ዲሳሳ ሳጥን ውስጥ ቢኒያም ዐይተን ላይ የሠራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠው የፍጹም ቅጣት ምት ቢንያም አይተን አስቆጥሮ አዳማ ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል።

ባህር ዳሮች 30ኛው ደቂቃ ላይ በወንድወሰን በለጠ አዳማዎች ደግሞ 38ኛው ደቂቃ ላይ በዳዋ ሆቴሳ አማካኝነት ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን 45+1ኛው ደቂቃ ላይ አዳማዎች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ቢኒያም ዐይተን ከቀኝ መስመር ባሻገረው ኳስ አቡበከር ሳኒ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ቢቀጥልም የጣና ሞገዶቹ 64ኛው ደቂቃ ላይ የማሸነፊያ ግብ አስቆጥረዋል። አንተነህ ተፈራ ከሳጥን አጠገብ በግራ እግሩ በግሩም ሁኔታ መሬት ለመሬት የመታው ኳስ ግብ ሆኖ ባህር ዳሮችን ወደ ድል የመለሰው ጨዋታ 2ለ1 ተጠናቋል።