ኢትዮጵያ መድን በወልዋሎ ላይ ቅሬታ አቀረበ፤ “ያቀረቡት አምስት ነጥብ መሠረተ-ቢስ አሉባልታ ነው” ክለቡ

የኢትዮጵያ መድን እግር ኳስ ክለብ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 37ኛ ሳምንት ከሽረ ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ ከአቅም በታች ተጫውቷል” በሚል ስሜን አጥፍቷል ባለው የወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ላይ ለሊጉ ውድድርና ሥነሥርዓት ኮሚቴ ይፋዊ የክስ እና የእርማት ደብዳቤ አስገብቷል።
ወልዋሎ ለኮሚቴው ባስገባው የቅሬታ ደብዳቤ፣ መድን በሽረ 3ለ0 የተሸነፈበት ጨዋታ ጥርጣሬ የፈጠረ መሆኑን ገልጾ እንደ ማሳያ አምስት ነጥቦችን አስቀምጦ ነበር። ኢትዮጵያ መድን በሥራ አስኪያጁ አቶ ይግዛው ብዙዓየሁ አማካኝነት በሰጠው ምላሽ ውንጀላው በስሜትና በግምት ላይ የተመሰረተ “የስም ማጥፋት ተግባር” መሆኑን በመግለጽ የወልዋሎን አምስት ማሳያ ነጥቦች በሕግ፣ በደንብና በማስረጃ እንደሚከተለው አጣጥሏቸዋል፦
1. “ሦስት ጎል ማስተናገዱ ጥያቄ ያስነሳል” ስለተባለው
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ጠንካራ የሚባሉ ክለቦች ጭምር 3 እና ከዚያ በላይ ጎል ተቆጥሮባቸው እንደሚሸነፉ የገለጸው መድን፤ ክለቡ ከዚህ ጨዋታ በፊት በነበሩት 36 ጨዋታዎች 10 ጊዜ መሸነፉን ጠቅሶ፣ በ37ኛው ሳምንት መሸነፉ ምን የሚያስጠረጥር? ነገር እንዳለው ጠይቋል።
2. “ዋና አሰልጣኙ ከጨዋታው በኋላ መግለጫ አልሰጡም” ስለተባለው
የክለቡ ዋና አሰልጣኝ በዕለቱ በሕመም ምክንያት ሕክምና ላይ እንደነበሩ ያሳወቀው ክለቡ፤ በሊጉ የውድድር ደንብ መሠረት ረዳት አሰልጣኙ በቦታው ተገኝተው ሕጋዊ መግለጫ በሰጡበት ሁኔታ ይህንን ለጥርጣሬ መነሻ ማድረግ ከንቱ ስም ማጥፋት ነው ብሏል።
3. “አመራሮቹ ከጨዋታ በኋላ ያሳዩት ምላሽ” ስለተባለው
የመድን አመራሮች ሁልጊዜም ቡድናቸውን ለመደገፍ ሜዳ እንደሚገኙና በቀጥታ ስርጭት መታየታቸው ሊያስመሰግናቸው እንጂ ሊያስጠረጥራቸው እንደማይገባ ገልጾ፤ “በቀጥታ ስርጭት የሚታዩ ምስሎች ምላሽን እንዴት እንደሚያሳዩ ክለቡ ያለውን ዕውቀት ቢያካፍለን ለመማር ዝግጁ ነን” ሲል በደብዳቤው ጠይቋል።
4. “የጎሎቹ አቆጣጠር እና የቀደሙት አምስት ጨዋታዎች አፈፃፀም” ስለተባለው
ይህ ውንጀላ ግልጽነት የሌለውና በማስረጃ ያልቀረበ መሆኑን የጠቀሰው መድን፣ የሌላ ክለብን እንቅስቃሴ ማንኳሰስና ማሳነስ የስፖርታዊ ጨዋነት መርህን ስለሚጥስ በዲሲፕሊን ሊያስጠይቅ እንደሚገባ አሳስቧል።
5. “ዓመቱን ሙሉ ያልተጫወተ 3ኛ በረኛ አሰልፈዋል” ስለተባለው
ክለቡ ነባራዊውን ተጨባጭ ሁኔታ አስረድቷል፦
1ኛ ግብ ጠባቂው 5 ቢጫ ካርድ በማየቱ መሰለፍ አልቻለም።
2ኛው ግብ ጠባቂ በጉዳት ላይ ከመሆኑም በላይ በፈቃድ ላይ ነበር።
ሕጉ ሜዳ ላይ ግብ ጠባቂ መኖር እንዳለበት ስለሚደነግግ 3ኛው ግብ ጠባቂ ተሰልፏል። ይህ ተጫዋች ደግሞ ወጣት ከመሆኑ ባለፈ በኢንተርናሽናል ውድድሮችም ጭምር ለክለቡ የተጫወተ መሆኑን ገልጾ፣ ወልዋሎ የጠቀሰው የፊፋ ሕግ አንቀጽ 18 በየትኛው ሕግ ላይ እንዳለ ጠይቋል።
መድን በመጨረሻም ባነሳቸው ጥያቄዎች
የዕለቱ የውድድር ገምጋሚዎች ክለቡ ከአቅም በታች ተጫውቷል የሚል ምንም ዓይነት ሪፖርት ባላቀረቡበት ሁኔታ ወልዋሎ ያቀረበው ውንጀላ የፍትሐዊነት ውድድርንና የኢትዮጵያን እግር ኳስ ተአማኒነት የሚጎዳ ነው ያለው መድን፣ የዲሲፕሊን ኮሚቴው የሚከተሉትን ውሳኔዎች እንዲያስተላልፍ ጠይቋል።
የቀረበው መሠረተ-ቢስ ውንጀላ በጥብቅ እንዲመረመር። ወልዋሎ ክሱን የሚደግፍ ተጨባጭ ማስረጃ እንዲያቀርብ እንዲታዘዝ (መድን ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ተጠያቂ ለመሆን ዝግጁ መሆኑን ገልጿል)
ክሱ ሀሰተኛና ስም ለማጥፋት የቀረበ ሆኖ ከተገኘ፣ በፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊን መመሪያ መሠረት በወልዋሎ ላይ ጠንካራ የዲሲፕሊን እርምጃ እንዲወሰድ ፣ ኢትዮጵያ መድን ለሚያስፈልገው ማንኛውም ምርመራ ሙሉ ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ ደብዳቤውን አጠቃሏል።

