በ2018 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስታዲየም የገቡ ደጋፊዎች ቁጥር ስንት ነው?

በ2018 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስታዲየም የገቡ ደጋፊዎች ቁጥር ስንት ነው?

ዓምና ስታዲየም ገብተው የሊጉን ጨዋታዎች የተከታተሉ ደጋፊዎች ቁጥር እንዲሁም ክለቦች ከስታዲየም ትኬት ያገኙት ገቢ ይፋ ሆነ።

የ2019 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእጣ ማውጣት መርሐ ግብር ከደቂቃዎች በፊት የተከናወነ ሲሆን ከእጣ ማውጣቱ በፊት የሊጉ የበላይ አካል የሆነው አክሲዮን ማኅበር ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ስላለፈው አመት እንዲሁም ስለዘንድሮው የውድድር ዓመት መጠነኛ ሀሳቦችን አንስተዋል። ስራ አስኪያጁ በዋናነት ከኮቪድ ወዲህ ሊጉ እየተደረገበት ያለውን ፎርማት አንስተው አምና ሊጉ መጠነኛ ጥናት አከናውኖ በተሰበሰበ ግብረ መልስ ክለቦች ከደጋፊዎቻቸው እየራቁ መምጣታቸውን በመገንዘብ ባሳለፍነው ግንቦት ወር ክለቦች ውድድር ማድረግ የሚፈልጉባቸውን ሜዳዎች እንዲመርጡ እንደተደረገና ቦርዱ የተመረጡትን ሜዳዎች ገምግሞ ለዘንድሮ የውድድር ዓመት 7 ስታዲየሞች እንደተመረጡ አመላክተዋል።

ታዲያ ስራ አስኪያጁ ይህንን ሀሳብ እያስረዱ ባለበት ወቅት በ2018 ስታዲየም ተገኝተው ጨዋታዎችን የተከታተሉ ደጋፊዎችን ቁጥር ጠቅሰዋል። በዚህም ባሳለፍነው ዓመት አጠቃላይ ከተደረጉ 380 ጨዋታዎች 291,665 ደጋፊዎች ትኬት ቆርጠው ስታዲየም እንደገቡ አመላክተዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ 32,481,351 ብር ከስታዲየም ትኬት ገቢ እንደተገኘ ገልፀዋል።

ስራ አስኪያጁ አቶ ክፍሌ በዘንድሮ አመት በሚደረጉት 7 ሜዳዎች ይህ ቁጥር እንደሚያድግ እንደሚጠበቅና በ2020 ደግሞ ወደ መደበኛ የሜዳ እና የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች ሲኬድ የተሻለ የደጋፊ ቁጥር እንደሚመዘገብ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።