የፊታችን እሁድ የሚደረገውን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫን በተመለከተ ገለፃ ተሰጥቷል።

ከቆይታዎች በፊት የኢትዮጵያ ከፍተኛውን የሊግ እርከን ውድድር የሚመራው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር መስከረም 29 የሚጀምረውን የሊጉን ውድድር ድልድል ያወጣ ሲሆን ጎን ለጎን የፊታችን እሁድ ስለሚደረገው የአክሲዮን ማኅበሩ 8ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ እና የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ ሀሳቦች ተነስተዋል።
ስለጉዳዩ ማብራሪያ የሰጡት የአክሲዮን ማኅበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ተቋማቸው እንደ ማንኛውም የአክሲዮን ማኅበር የንግድ ተቋም በየአመቱ ጠቅላላ ጉባኤ የሚያካሂድ መሆኑን ገልፀው የፊታችን እሁድም በጠቅላላ ጉባኤው የአመቱ ሪፖርቶች እና የአዲሱ ዓመት ዕቅዶች እንደሚቀርቡ አመላክተዋል። በዋናነት ደግሞ በመጪዎቹ ሦስት አመታት ሊጉን በአመራርነት የሚያገለግሉ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ እንደሚካሄድ ተናግረው ምርጫው የሚካሄድበትን ሂደት በተመለከተ ተከታዩን ገለፃ አድርገዋል።
ስራ አስኪያጁ እንዳብራሩት በሊጉ የሚወዳደሩ 18ቱም ክለቦች እጩዎችን የሚያቀርቡ ሲሆን ክለቦች የሚያቀርቧቸው አንድ አንድ እጩዎች በአሁኑ ሰዓት በክለቡ ውስጥ እያገለገሉ ካሉ ፕሬዝዳንት፣ ስራ አስፈፃሚ አባላት እንዲሁም ስራ አስኪያጆች መካከል ብቻ እንደሆነ ጠቅሰዋል። አቶ ክፍሌ ገለፃውን እያደረጉ በነበረበት ጊዜ ወደ 14 የሚጠጉ እጩዎች እንደተላኩ አመላክተው የእጩ ማስገቢያ ቀን ዛሬ እንደሚያበቃም ተናግረዋል።
በምርጫ ሂደቱ ላይ ጠቅላላ ጉባኤው አስመራጮችን እዛው የሚሰይም መሆኑ ከመድረኩ ሲገለፅ ምናልባት ጉባኤው አስመራጮችን የማይመርጥ ከሆነ ስራ አስኪያጁ በአስመራጭነት እንደሚያገለግሉ በደንቡ እንደተቀመጠ ተነግሯል። አስመራጩ አካል ከተመረጠ በኋላም በግልፅ ሁኔታ ክለቦች የወከሏቸው አካላት ከመጡበት ክለብ ጋር በስክሪን እየታየ መረጣው እንደሚከናወን የተብራራ ሲሆን መራጭ ክለቦችም 7 ሰዎችን ብቻ የመምረጥ መብት እንዳላቸውና ከ7 በላይ ሰዎችን እንደማይመርጡ ከዛ በታችን ግን መምረጥ እንደሚችሉ ተመላክቷል።
ምርጫው በዚህ ሂደት ቀጥሎ ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ብዙ ድምፅ ያገኙ ሰዎች በዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት እንደሚመረጡና ከ20 % በላይ ድምፅ ያገኙ ነገር ግን 8ኛ እና 9ኛ የሆኑ ሰዎች በተጠባባቂነት እንደሚያዙ ተብራርቷል። ሰባቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ በዚህ መንገድ ከተመረጠ በኋላ የተመረጡት ሰዎች ራሳቸው ተመካክረው ሰብሳቢ እና ምክትላቸውን እንደሚሰይሙ አቶ ክፍሌ በንግግራቸው ጠቁመዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደ ሌሎች የስፖርት ፌዴሬሽኖች የምርጫ ዘመን ገደብ በአክሲዮን ማኅበሩ እንደሌለ ታውቋል።

