ታክቲካዊ ትንታኔ ፡ መከላከያ 2-0 ወልድያ

እሁድ በተደረገው የ9ኛ ሳምንት ጨዋታ የገብረመድህን ኃይሌው መከላከያ ወልድያን በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል፡፡ የሶከር ኢትዮጵያው ሚልኪያስ አበራ ጨዋታውን ተመልክቶ የመከላከያን የድል ምስጢርና የጨዋታውን አንኳር ታክቲካዊ ጉዳዮች እንዲህ ተንትኖታል፡፡

 

በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ከሚገኙት ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው የአሰልጣን ገብረመድህን ኃይሌው መከላከያ በሜዳው ያደረገውን የ9ኛ ሳምንት ጨዋታ ዘንድሮ በአብዛኛው እየተጠቀመበት ባለው የ4-4-2 የተጫዋች የሜዳ ላይ አደራደር (ፎርሜሽን) የጀመረ ሲሆን የፕሪሚየር ሊጉ እንግዳ ወልድያ አሰልጣኝ ሚልዮን ታዬ ደግሞ 4-1-4-1 ተጠቅሟል፡፡

ምስል 1

 

የመጀመርያው አጋማሽ

መከላከያዎች ከወትሮው በተለየ በዚህ ጨዋታ ጠንቃቃ ሆነው ታይተዋል፡፡ ሁለቱም የመስመር ተከላካዮች ከመሃል ተከላካዮች ሳይርቁ ሲንቀሳቀሱ ነበር፡፡ በተጋጣሚ ሜዳ (በወልድያ የሜዳ ክልል) የተስተዋሉትም ለጥቂት ጊዜያት ብቻ ነው፡፡ የፊተኛውን መስመር ለመጠቀም ሽመልስ ተገኝ (2) የተሻለ ሲጥር (Overlap) ሲያደርግ ነበር፡፡ የወልድያዎቹ አክሌስያስ ግርማ (21) እና አንሳር መሃመድ (19) ወደኋላ ተጠግተው ፉልባኮቻቸውን በመከላከል ስራ ሲያግዟቸውና መስመሩ ላይ የቁጥር ብልጫ በመውሰድ (overload በማድረግ) መከላከያ በመስመሮች የሚደረግ ፈጣን ከመከላከል ወደ ማጥቃት የሚደረግ ሽግግር ( quick flack transition) ሲገቱባቸው ውለዋል፡፡ በእርግጥ መከላከያ ተደጋጋሚ የቦታ ለውጥ በሚፈጥሩበት የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቾቹ ሙሉአለም (18) እና መሃመድ (17) ተጭኖ ለመጫወት ሞክሯል፡፡ ይህም በ31ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቶ በጨዋታው በሁለገብነት ሚና በተለያዩ የሜዳ ክፍሎች ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አምበሉ ሚካኤል ደስታ (13) በግራው መስመርና ከ9 ቁጥሩ ጋር በፈጠረው አንድ ሁለት ቅብብል የወልድያን የመከላከል ቅርጽ በማሳት የተሸማችን ኳስ ተስፋዬ በቀለ (11) የመጀመርያውን ግብ እንዲያስቆጥር አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

ወልድያዎች የመሃለኛው ክፍል ላይ የነበራቸው ትኩረት አናሳ ከመሆኑ አንፃር መከላከያዎች በመሃል ተከላካዮቻቸው ሳይቀር በሜዳው ቁመት የመሃሉን ክፍል ለመጠቀም ሲሞክሩ የታዩትም ለዚህ ይመስላል፡፡ ተጫዋቾቹ ከፊት ለፊታቸው የሚያገኙትን ሰፊ ክፍተት (የወልድያ አማካኞች ለተከላካዮቻቸው እጅግ ቀርበው በመጫወታቸው ከፊት ለፊታቸው ሰፊ ክፈተትን ይተዉ ነበር) ለተጫዋቾቻቸው የመቀባበያ አማራጮችን የሚያዘጋጁበትን ጊዜም ይሰጣቸው ነበር፡፡ ተጠቅጥቆ በሚከላከለውና አንድ አጥቂን በፊት መስመር በራቀ አቋቋም ላይ ባስቀመጠው ወልድያ ላይም መከላከያ ረጃጀም ኳሶችንና ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶችን (through balls) መጠቀሙ ለ2ኛው ጎል እንደ ምክንያት መጠቀስ ይችላል፡፡ መሃመድ ከተከላካዮቹ ጀርባ በወልድያ የመሃል ተከላካይ ታደለ ባይሳ(5) እና ቀኝ ፉልባኩ ነጋ በላይ (18) መካከል ያለፈችን ኳስ ሲያሸንፍ በተፈፀመበት ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ መሃመድ በ36ኛወ ደቂቃ ላይ ከግቡ አግዳሚ ጋር አላትሞ ወደ ግብነት ቀይሮታል፡፡ በመከላከያ 2-0 መሪነትም ለእረፍት ወጥተዋል፡፡ (ምስል 2)

Mekelakeya 2-0 Woldia (2)

2ኛው 45

በዚህኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ወልድያዎች የተሸለ ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል፡፡ በመከላከያ በኩል የተደረገው የተጫዋች ቅያሪ (ዮሃንስ ኃይሉ በአወል ተቀይሮ ገብቷል) የሚና ልዩነትን ለመጠቀም አስችሏቸዋል፡፡ ተቀይሮ የገባው ዮሃንስ ‹‹ ኩባ ›› በአብዛኛው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት (attacking phase) ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ስለሚያደርግ ትቶት የሚሄደውን ቦታ የወልድያው አንሳር መሃመድ ሲጠቀምበት ነበር፡፡ በዚህ መስመር ወልድያ ጫና ማሳደሩም የዚህኛው እንቅስቃሴ ውጤት ማሳያ ተደርጎ ሊታሰብ ይችላል፡፡ የወልድያው ወሰኑ ማዜ (20) ጥሩ የፊት ለፊት ሩጫ ከኳስ ጋር ማድረጉ ለቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ አይነተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ የቡድኑ ችግር ከመከላከል ወደ ማጥቃት በሚያደርገው ሽግግር ( Attacking Transition ) ላይ በተጋጣሚ የሜዳ ክልል ላይ ብዙ ተጫዋቾችን ማሳተፍ አለመቻሉ ነው፡፡ በተጨማሪም የተጫዋቾች ቦታን ጠብቆ የመጫወት ብቃት (Positional Play) እምብዛም ነበር፡፡

የመከላከያዎቹ የመሃል ተከላካዮች የነበራቸው ጨዋታን የማንበብና በተደራጀ መልኩ የመከላከል ስርአት የቡድኑ ጠንካራ ጎን ነበር፡፡ ፉል ባኮች ሊሊጠቁ ወደ ፊት ሲሄዱ ወደ መስመር በመጠጋት ክፍተቱን ለመሙላት ያደረጉት የተደራጀ የመከላከል ስልት ሊያስመሰግናቸው የሚገባ ነው፡፡ ሁለቱ የመከላከያ ተከላካዮች (ሲሳይ ደምሴ እና ተስፋዬ በቀለ) ከዚህ ቀደም በመስመር ተከላካይነት ሚና ተጫውተው ማለፋቸው ኳስን በምቾት ወደፊት ይዘው እንዲሄዱ ሳያበረታቸው እንዳልቀረ ይገመታል፡፡ ሳሙኤል ታዬ (19) እና 9 ቁጥሩ ከመስመር ወደ ውስጥ እየገቡ የመሃል ሜዳ የበላይነት ለማስገኘት ያደረጉት ጥረት ለተጋጣሚ ቡድን የጎንዮሽ ክፍተትን ቢፈጥርም ያን ያህል አስጊ የሆነ የግብ ሙከራ አልተደረገባቸውም ፡፡ ሌላው መጠቀስ ያለበት ነገር ቢኖር ጀማል ጣሰው የዘመናዊው እግርኳስ አለም ግብ ጠባቂዎች ተፈላጊ ሚናን በመተግበር የሚያሳየው እንቅስቃሴ ነው፡፡ ግብ ጠባቂው ቡድኑ Highline Defense በሚሰራበት ወቅት (ወደ መሃል ተጠግቶ በሚከላከልበት ወቀት) ከግቡ ራቅ ብሎ በመገኘት ከተከላካዮቹ ጀርባ የሚላኩ ኳሶችን መመለስ መቻሉ ነው፡፡ ጥንቃቄ የታከለበት ብስለትን የሚፈልገው ይህ እንቅስቃሴ በጥሩ የታክቲክ ልምምድ ከታገዘ ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡

ምስል 3

Mekelakeya 2-0 Woldia (3)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *