በሊጉ 9ኛ ሳምንት ሲዳማ ቡና መሪነቱን ሲያጠናክር ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አናት እየተጠጋ ነው

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቅዳሜ እና እሁሁ በተደረጉ የ9ኛ ሳምንት ጨዋታዎች መሪው ሲዳማ ቡና ፣ መከላከያ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ድል ቀንቷቸዋል፡፡

ሲዳማ ቡና (ፎቶ በኢትዮ ቲዩብ)
ሲዳማ ቡና (ፎቶ በኢትዮ ቲዩብ)

ቅዳሜ አዲሰስ አበባ ስታድየም ላይ ሀዋሳ ከነማን ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡ ሀዋሳ ከነማዎች ታፈሰ ተስፋዬ ገና በ5ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ እስከ 85ኛው ደቂቃ ድረስ 1-0 መምራት ቢችሉም አቢኮዬ ሻኪሩ በሀዋሳ ከነማ የግብ ክልል ውስጥ በተሰራበት ፋት የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ቢንያም አሰፋ ወደግብነት ቀይሮ ኢትዮጵያ ቡና ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ አድርጓል፡፡

ቅዳሜ በተካሄደው ቀጣይ ጨዋታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውጤት አልባ ጉዞው ገፍቶበታል፡፡ በ11፡30 አዳማ ከነማን ያስተናገደው ባንክ አብዱልከሪም ሃሰን ባስቆጠረው ግሩም ግብ 1-0 ሲመራ ቆይቶ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 1 ደቂቃ ሲቀረው ቢንየም አየለ ባስቆጠረው ግብ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡

እሁድ 5 ጨዋታዎች የተካሄዱ ሲሆን በ9 ሰአት ሲጠበቅ የነበረው የሲዳማ ቡና እና የወላይታ ድቸ ፍልሚያ በይርጋለሙ ክለብ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ የሲዳማን ሁለት የድል ግቦች ኬንያዊው ኤሪክ ሙራንዳ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ሲዳማ ድሉን ተከትሎ መሪነቱን ሲያጠናክር ወላይታ ድቻ ከ4 ተከታታይ ድሎች በኋላ ሽንፈት አስተናግዷል፡፡

አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ወለድያ ከነማን ያስተናገደው መከላከያa 2-0 በማሸነፍ 2ኛ ደረጃን ከመብራት ኃይል ተረክቧል፡፡ የጦሩን የድል ግቦች ያስቆጠሩት ተስፋዬ በቀለ እና መሃመድ ናስር በፍፁም ቅጣት ምት ነው፡፡

ትላንት በተመሳሳይ 9፡00 በተደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች አሰላ ላይ ሙገር ሲሚንቶ ደደቢትን አስተናግዶ በጌድዮን አካፓ እና ኤፍሬም ቀሬ ግቦች 2-1 በሆነ ውጤት ሲረታ ጎንደር ላይ ዳሽን ቢራ አርባምንጭ ከነማን በየተሻ ግዛው ግብ 1-0 አሸንፎ ደረጃውን አሻሽሏል፡፡

ብዙዎች በጉጉት የጠበቁት የዚህ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ 11፡30 አዲስ አበባ ሰታድየም ላይ ተካሂዶ ቅዱስ ጊዮርጊስ መብራት ኃይልን 1-0 በማሸነፍ 3ኛ ደረጃን ከወላይታ ድቻ ተረክቧል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስን የማሸነፍያ ግብ አዳነ ግርማ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሯል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደካማ አጀማመር በኋላ ወደ ቀድሞ አሸናፊነት በመመለስ ከመረው ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ሁለት ሲያጠብ በውድድር ዘመኑ ሽንፈት ሳያስተናግድ የቆየው መብራት ኃይል የመጀመርያ ሽንፈቱን አስተናግዷል፡፡

ፕሪሚየር ሊጉን ሲዳማ ቡና በ17 ነጥብ ሲመራ መካላከያ በ16 ፤ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ15 ይከተላሉ፡፡ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ሰንጠረዥ ቢንያም አሰፋ በ7 ግብ ሲመራ ሳሚ ሳኑሚ በ6 ይከተላል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *