ታክቲካዊ ትንታኔ ፡ መብራት ኃይል 0-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

 

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ መብራት ኃይልን በመርታት 3ኛ ደረጃን ተረክቧል፡፡ የሶከር ኢትዮጵያው ሚልኪያስ አበራ በጨዋታው የተከሰቱ ታክቲካዊ ጉዳዮች እነዲህ ተመልክቷቸዋል፡፡

 

ከሳምንቱ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጠባቂ ፍልሚያዎች አንዱ በሆነው በዚህ ጨዋታ የባለሜዳነቱን ተራ ወስዶ የገባው መብራት ኃይል 4-4-2ን የቡድኑ መነሻ ፎርሜሽን አድርጓል፡፡

በብራዚላዊው የቀድሞ የጃሜይካ ብ/ቡድን አሰልጣኝ ኔይደር ደ ሳንቶስ ስር ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ የመጣው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ውጤት እያስመዘገበበት ባለው 4-3-3 አጨዋወት ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡ (ምስል 1)

 

የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ይዘት

የአሰልጣን አጥናፉ ቡድን የቅዱስ ጊዮርጊሶችን የመስመር ተከላካዮችን (ዘካርያስ እና ቢያድግልኝ) የማጥቃት እንቅስቃሴ (overlapping movement) ለመግታት የቀደ ይመስላል፡፡ የፈረሰኞቹ ግራ መስመር ከቡድኑ ጠንካራ ጎኖች አንዱ ስለመሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም፡፡ በብዙ ጨዋታዎች እንደተመለከትነው ዘካርያስ ዘመናዊ የመስመር ተከላካይ ነው፡፡ እንቅስቃሴዎቹም ጊዜያቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ያለው ተሳትፎም ቀጥተኛ ነው፡፡ ለአማካዮች እና ለአጥቂዎች የመቀባበያ አማራጮችን ሲሰጥ ከመስመር የሚልካቸው ልኬታቸውን የጠበቁ ተሻጋሪ ኳሶቹ ብልሃትና ብልጠት የታከለባቸው ፣ ኳስን የማስጣል ስልቶቹም ከተጫዋቹ ጠንካራ ጎኖች መካከል ናቸው፡፡ ዘመነዊ የሆነው የማጥቃት እና የመከላከል አጨዋወቱ በደጋፊዎችና በአሰልጣኞች እንዲወደድ ያደረገው ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡

የዚህን ተጫዋች ሚና መገደብ መቻል የተጋጣሚው ቡድን አሰልጣኞች የቤት ስራ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አሰልጣኝ አጥናፉ በአጥቂያቸው ራምኬል ሎክ እና በቀኝ መስመር አማካኛቸው አዲስ ነጋሽ አማካኝነት ዘካርያስን ከቦታው ብዙም ርቆ እንዳይወጣ ተጭነውት እንዲጫወቱ ማስደረጋቸው የዚህ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ የመብራቱ አዲስ ነጋሽ ቦታን ጠብቆ የመጫወት ስርአት (Positional Play) ላይ ያለው አቋም ደካማ ነው፡፡ መስመሩን ከመጠቀም ይልቅ ወደ መሃል ሲገባ ከኋላው ያለው የመስመር ተከላካይ (አወት) ይበልጥ ተጋላጭ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በተጨማሪም የመብራት ኃይል የመስመር ተከላካዮች እና የመሃል ተከላካዮቹ በአብዛኘው የሚታዩት በአንድ መስመር በመጫወት ነው፡፡ ይህ አጨዋወት ደግሞ ፊታቸው ካሉት ጋር ካሉት አማካኞች እጅግ ያርቃቸዋል፡፡ አማካዮቹም ወደኋላ እንዲመለሱና ሰፊ ክፍተትን እንዲሸፍኑ ያስገድዳቸዋል፡፡ ይህም ሳይሆን አይቀርም ራምኬል በጨዋታው ከማጥጥት ሰፍራው ይልቅ ወደ መስመር ሲጠጋ እንድናስተውል ያደረገን፡፡

የቻምፒዮኖቹ High Line Defence (ወደ አማካይ መስመር ተጠግቶ በመከላከል) በመስራትና በመስመሮቻቸው መካከል ያሉትን ክፍተቶች በማጥበብ ተጋጣሚያቸው የመቀባበያ አማራጭንና የማጥቃት ማእዘናትን እንዳያገኝ አድርገዋል፡፡ የቀድሞው የቡና አማካይ ፋሲካ አስፋው በሁለገብነት ሚና በሁለቱም መስመሮች እየተመላለሰ ለጓደኞቹ የሶስት ማእዘን የመቀባበያ አማራጮችን ሲፈጥር ተስተውሏል፡፡ ከናትናኤል ዘለቀ ትይዩ በመሆንም የመከላከል ሃላፊነትን ሲወጣ ነበር፡፡ ምንያህል እና በሃይሉ ወደ ፊት እና ወደኋላ መበንቀሳቀስ በሁለቱም የጨዋታ ሂደቶች (Playing Phases) ማጥቃት እና መከላከል ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ ምንያህል የግራ ፉልባኩ ዘካርያስ ላይ ጫና በመደረጉ ወደ ኋላ አፈግፍጎ ተገዷል፡፡ ይህም አጥቂው ፍፁምን ይበልጥ ወደ ቀኝ መስመር እንዲያደላ አድርጎታል፡፡ ፍፁም በሁለቱም ክንፎች ጫና ማሳደር መቻሉ ቡድኑ በ22ኛው ደቂቃ ላይ ለተገኘው ፍፁም ቅጣት ተዘዋዋሪ የሆነ ሚና ነበረው፡፡ አዳነ ወደ ኋላ እየተመለሰ በመጫወቱ የመብራት ኃይሎችን የመሃል ተከላካዮች ቅርፅ ሲያበላሽ ነበር፡፡ ይህም የመሃል ተከላካዩ ሲሴ ከጀርባው የተላከን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ( through ball ) ለማዳን ባደረገው ጥረት የፈፀመው ያልተገባ ጨዋታ አዳነ ላስቆጠረው የፍፁም ቅጣት ምት ምክንያት ሆናለች፡፡ጊዮርጊስም 1-0 እየመራ እረፍት ሊወጣ ችሏል፡፡ (ምስል 2)

 

ምስል 1
ምስል 1

2ኛ አጋማሽ

የጊዮርጊሶች Squeezing Play

ቡድኑ የመስመር አማካኞቹን ቦታ እየቀየረ ከመጫወቱ በተጨማሪ በእያንዳንዱ የተጫዋች መስመር መካከል ያለውን ክፍተት አጥብቦ በመጫወት ተጋጣሚዎቹን ተጭኖ ሲጫወት አምሽተዋል፡፡ ይህ አጨዋወት በትክክል ሲተገበር ቡድኑ ከመከላከል ወደ ማጥቃትም ይሁን ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚያደርገው ሽግግር ተጫዋቾቹ ብዙ ርቀት እንዳይጓዙና ብዙ ጊዜ እንዳይወስድባቸው ያግዛቸዋል፡፡ በማጥቃት እንቅስቃሴ በተጋጣሚ ሜዳ ብዙ ተጫዋቾች እንዲሳተፉም ያስችላቸዋል፡፡ ተስፋዬ አለባቸው ተቀይሮ ሲገባ የታየው ይህ ነው፡፡ ሙሉ የተከላካይ መስመሩ ስቦ ወደላይኛው ሜዳ ሲያስጠጋቸው ታይቷል፡፡ የሚቆሙ ኳሶችን ወድያው ለማስጣል የሚደረገው አድካሚ ጥረትም ይቀንሳል፡፡ ይህ የጊዮርጊስ አጨዋወት የመብራቶቹ ወንድሜነህና ፍቅረየሱስ ይበልጥ ወደመሃል እንዲገቡ ሲያስገድዳቸው ታይቷል፡፡ (ምስል 3)

Electric 0-1 Giorgis (3)

የመብራት ኃይል Box Midfield

የአሰልጣኝ አጥናፉ የታክቲክ እይታና መፍትሄዎቻቸው ፈጣኖችና የታቀደባቸው ናቸው፡፡ ፈረሰኞቹ ሜዳን አጥብቦ የመጫወት ስልት ለማስቀረት የወሰዱት እርምጃ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ቡድኑ ለወሰደው የበላይነት ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ አሰልጣኙ ቡድኑ በፍላት ሚድፊል (በአንድ ቀጥታ የጎንዮሽ መስመር) ሲጫወት የነበረውን አጨዋወት በመቀየር እንዲሁም ለዚህ ስልት እጅግ አመቺ የነበረውን ተጫዋች ወደ ሜዳ በማስገባት ፍቅረየሱስ የመሃል ክፍል ቅርፃቸው የባለሁለት መስመር የሳጥን ቅርፅ አስይዘውት ጊዮርጊሶች ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ አድርጓቸዋል፡፡ ይህም ለመብራት ኃይል Depth (ጥልቀት) እንዲሰጥና የሜዳውን ቁመት ለመጠቀም እንዲችሉ አድርጓል፡፡ በእርግጥ ዘዴው ለተጋጣሚ ቡድን የሜዳ ወርድ ጥቅም (Width) ሊያስገኝ ቢችልም አሰልጣኙ ፉልባኮችን የበለጠ ወደፊት በማስጠጋት የአጨዋወቱን ችግር ሊቀርፉ ችለዋል፡፡ በዚህም አማካኝነት በሁለቱም መስመሮች ፈጣን የሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር፡፡ በተደጋጋሚ የግብ ማግባት ሙከራዎችንም አድርገዋል፡፡ በተለይም በቀኝ መስመር በኩል ፍቅረየሱስ ፣ ዮርዳኖስ አባይ እና አወት ገ/ሚካኤል መስመሩን overload በማድረግ (የቁጥር ልጫ በመውሰድ) ጊዮርጊሶችን ጫና ውስጥ ከተው አምሽተዋል፡፡

የመብራት ኃይሉ አሰልጣኝ ውጤት ባይቀናቸውም ከፈጣን የታክቲክ ለውጥ እርምጃ እና ከጥሩ ጨዋታ የማንበብ ብቃት እንዲሁም ትክክለኛ ተጫዋችን ከመቀየር ውሳኔ ጋር በተያያዘ የሚፈጥሩትን ለውጥ ሳላደንቅ አላልፍም፡፡ (ምስል 4)

ምስል 4
ምስል 4

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *