ሽረ ምድረ ገነቶች ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ሲመለሱ ድሬድዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ያለግብ ተለያይተዋል

ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
የመጀመሪያው አጋማሽ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በነበራቸው ድሬዳዋ ከተማዎችና ጥቃትን መሠረት ባደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች መካከል መጠነኛ ፉክክር ያሳየን ነበር። በተለይም ቡናማዎቹ በዘላለም አባተ እና በአቡበከር አዳሙ አማካኝነት ወደ ግብ ክልል ተደጋጋሚ ጉብኝቶችን በማድረግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን መሰንዘር ቢችሉም ኳሶቹ ኢላማቸውን ባለመጠበቃቸው ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ከእነዚህ ጥቂት አጋጣሚዎች ውጪ ግን ሁለቱም ክለቦች ጥንቃቄን መርጠው በመጫወታቸው ጨዋታው ተጨማሪ የግብ ዕድሎችን ሳያስመለክተን በአቻ ውጤት ወደ ዕረፍት አምርቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች የጨዋታውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ይዘው ቢቀጥሉም ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን ተጠግቶ ጥራት ያላቸውን አደገኛ ሙከራዎች በመሰንዘር ረገድ ግን አሁንም ድክመት ይታይባቸው ነበር። በተቃራኒው ኢትዮጵያ ቡናዎች አልፎ አልፎ የሚያገኟቸውን አጋጣሚዎች ወደ ግብ ለመቀየር ጥረቶችን ሲያደርጉ ተስተውሏል በተለይም ቃልኪዳን ዘላለም ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታትንና ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳሁን ያዳነበት እንዲሁም ተቀይሮ የገባው በረከት ብርሃኑ መትቶ በግቡ ቋሚ የተመለሰበት ኳስ ቡናማዎቹን ለመሪነት አቅርበው ነበር።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተሰጡ ተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ሸምሰዲን የሰነዘረውን አደገኛ ሙከራ ጀሚል ያዕቆብ ከመስመር ላይ እንደምንም ባወጣበት አጋጣሚ ኢትዮጵያ ቡናዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በመሆኑም ሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር ያደረጓቸው ጥረቶች ሳይሳኩ ቀርተው ጨዋታው ያለምንም ግብ ዜሮ ለዜሮ በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ሽረ ምድረ ገነት ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ጨዋታው ገና ከጅማሮው በሁለቱም ክለቦች በኩል ፈጣን ሽግግሮችንና አስደናቂ የግብ ሙከራዎችን ያስመለከተ ነበር። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል በመጀመሪያዎቹ ሦስት ደቂቃዎች ውስጥ በአቤል ሀብታሙ እና በኢዮብ ገብረማርያም አማካኝነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ቢደረጉም ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል። በተቃራኒው ምድረ ገነት ሽረዎች በዳንኤል ዳርጌ አማካኝነት ፈታኝ ኳስ ቢሰነዝሩም የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ዮሱፍ ሞሮ ሊያድንበት ችሏል።
በአጋማሹ የተሻለ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ምድረ ገነት ሽረዎች በ21ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል። በኃይሉ ግርማ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ዳንኤል ዳርጌ አመቻችቶ ሲያቀብለው አንተነህ ተስፋዬ ኳሷን በአግባቡ ተጠቅሞ ወደ ግብነት በመለወጥ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ግብ ለማግኘት ከፍተኛ ጫና ቢፈጥሩም ምድረ ገነት ሽረዎች ውጤቱን ለማስጠበቅ ወደ ኋላ አፈግፍገው በመከላከል ተጫውተዋል። ኤሌክትሪኮች በቤዛ መድኅን እና በፍቃዱ አስረሳኸኝ አማካኝነት በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ለግብ እጅግ የቀረቡ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ጨዋታው በሽረ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ይህም ውጤት ምድረ ገነት ሽረ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ የመጀመሪያ ድሉን እንዲያከብር አስችሎታል።

