የ2018 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ሴቶች ከፍተኛ ሊግ ዛሬ ሰበታ ላይ ፍጻሜውን ሲያገኝ አስቀድሞ ቻምፒዮንነቱን ያረጋገጠው ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ ዋንጫውን ተረክቧል።

5:00 ላይ ጥሩነሽ ዲባባን ተከትሎ ወደ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ለማደግ በተመሳሳይ ሰዓት ጨዋታዎች ተደርገው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ አዲስ ከተማን የገጠመው ጉለሌ ክ/ከተማ 1-0 በማሸነፍ ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ ማደጉን አረጋግጧል። ሰበታ ላይ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ጨዋታውን ያደረገው ፋሲል ከነማ ደግሞ 1-0 ተሸንፎ ማደግ ሳይችል ቀርቷል። አንደኛውን ዙር በመሪነት አጠናቆ የነበረው ፋሲል ከተማ ከለሚ ኩራ ጋር እኩል 44 ነጥብ እና 16 የጎል ልዩነት በመያዝ በውድድሩ ደንብ መሠረት የተሻለ የስፖርታዊ ጨዋነት ነጥብ በመሰብሰቡ ሦስተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል።

9:00 ላይ በተደገረው የሊጉ የመዝጊያ ጨዋታ ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማን 4-3 በማሸነፍ አጨራረሱን አሳምሯል። ልዲያ ኢያሱ ሁለት ጎሎች ስታስቆጥር አምበሏ ልዲያ ሰሎሞን እና ረድኤት ዓለማየሁ ቀሪዎቹን አስቆጥረዋል።
ድሉን ተከትሎ ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ በ24 ጨዋታ 57 ነጥቦችን በመሰብሰብ ቻምፒዮን ሲሆን አጥቂዋ ልዲያ ኢያሱ ደግሞ በ19 ጎሎች ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን አጠናቃለች።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተካሄደው የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫ ጉለሌ ክ/ከተማ ሲሸለም የብር ሜዳልያ ጉለሌ ክ/ከተማ፣ የነሐስ ሜዳልያ ፋሲል ከነማ ተሸልመዋል። በመጨረሻም ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት አካዳሚ ዘንድሮ በአዲስ መልክ የተዘጋጀውን ዋንጫ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በመቀበል መርሐ ግብሩ ተጠናቋል።

