በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ የተገናኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አርባምንጭ ከተማ ሳይሸናነፉ 2 አቻ ተለያይተዋል፡፡ ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶች፣ ድንቅ ግብ፣ የእንግዶቹ የጨዋታ የበላይነት እንዲሁም አሳዛኝ ክስተት ያስተናገደ ጨዋታ ሆኖም አልፏል፡፡
ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ በ72 ዓመቱ አርብ እለት ላጣነው ጀግናው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት ተደርጓል፡፡
በመጀመሪያው አጋማሽ አዞዎቹ በተደጋጋሚ የሀምራዊዎቹን የተከላካይ መስመር መረበሽ የቻሉ ሲሆን ጨዋታው በተጀመረ በመጀመሪያው ደቂቃ ገብረሚካኤል ያቆብ ያገኘውን ኳስ ሳይጠቀምበት የንግድ ባንክ ተከላካዮች አውጥተውበታል፡፡
በአምስተኛው ደቂቃ በድንቅ አቋም ላይ የሚገኘው ወንድሜነህ ዘሪሁን አዞዎቹን ቀዳሚ ያደረገች ግብ ከአመለ ሚልኪያስ ኳስ ከተቀበለ በኃላ አስቆጥሯል፡፡ በግቧ መቆጠር የደቡብ ኢትዮጵያውን ክለብ የተነቃቃ ይመስል ነበር፡፡ የታደለ መንገሻ፣ የወንድሜነህ፣ የገብረሚካኤል እና አመለ ጥምረት እጅግ በጣም ስኬታማ ነበር፡፡
በ17ኛው ደቂቃ የሃምራዊዎቹ የመሃል ተከላካዩ አቤል አበበ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል፡፡ ከ13 ደቂቃዎች በኃላ ታዲዮስ ወርዴ በድንቅ ሁኔታ ከ20 ሜትር ርቀት በቮሊ የመታው ኳስ ጃክሰን ፊጣ መረብ ላይ አርፏል፡፡ ነገር ግን የንግድ ባንክ አቻነት የዘለቀው ለአምስት ደቂቃዎች ብቻ ነው፡፡ አመለ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሱ አመለ መትቶ የአዞዎቹን ሁለተኛ ግብ ከመረብ አዋህዷል፡፡ ሁለቱ ክለቦች ወደ መልበሻ ከማምራታቸው አስቀድሞ ከቅጣት ምት ጋናዊው አማካይ ጋብርኤል አህመድ ሞክሮ ጃክሰን አምክኖበታል፡፡
በሁለተኛው አጋማሽ ንግድ ባንኮች የመሃል ሜዳ ብልጫን ለመውሰድ በማሰብ የተጫዋች ለውጥ ቢያደርጉም አሁንም አርባምንጮች ተሽለው ታይተዋል፡፡ እንደመጀመሪያው አጋማሽ የጠሩ የግብ ማግባት ሙከራዎች ባይደረጉም አዞዎቹ በተደጋጋሚ በመልሶ ማጥቃት ወደ ተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል መድረስ ችለው ነበር፡፡ በ82ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂው ጃክሰን እና የንግድ ባንኩ የግራ መስመር ተከላካይ አንተነህ ገብረክርስቶስ ከመስመር የተሻማን ኳስ ለመውሰድ ጥረት ሲያደርጉ በመጋጨታቸው ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ሁለቱም ተጫዋቾች በአምቡላንስ ወደ ቤተዛታ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን ጨዋታው ለስምንት ደቂቃዎች ሊቋረጥ ችሏል፡፡ ጨዋታው ዳግም ሲጀመር ንግድ ባንኮች በ10 ተጫዋቾች ጨዋታወን ለማድረግ ተገደዋል፡፡
በ90+3ኛው ደቂቃ ንግድ ባንኮች ወሳኝ አንድ ነጥብ ማግኘት የቻሉበትን ግብ ማግኘት ችለዋል፡፡ ተቀይሮ በገባው ሞላለት ያለው ላይ በተሰራ ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አዲሱ ሰይፉ አስቆጠሮ ጨዋታው አንድ አቻ ተፈፅሟል፡፡
የአሰልጣኞች አስተያየት
ፀጋዬ ኪዳነማሪያም – ንግድ ባንክ
“በመጀመሪያው 10 እና 15 ደቂቃዎች አርባምንጭ የበላይነት ነበረው፡፡ ከምንም በላይ ትልቁ የአርባምንጭ ጥንካሬ መሃል ሜዳው ስለነበረ ያንን ጥንካሬ ግምት ውስጥ በማስገባት የመሃል ሜዳ ቁጥራችንን አብዝተን ለመጫወት ሙከራ አድርገን ነበር፡፡ በመጀመሪያው 45 የመሃል ሜዳ ስራችን የተወጣለት ስላልነበረ በነሱ የበላይነት ኳሱን እንዲቆጣጠሩ ስላደረጋቸው ሙሉ ለሙሉ መሃል ላይ ተብልጠን ነበር፡፡ ከዛ በኃላ የፎርሜሽን ለውጥ እና በመስመር ማጥቃት ምርጫችን አድርገን 3-5-2 ለመጫወት ሞክረናል፡፡ ተከላካያችን እምብዛም በሁለተኛው አጋማሽ የተጋለጠበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ”
” ፒተር ንዋዴኬ በግል ችግር እንዲሁም ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ከቋሚ 11 ውጪ መሆን ታዳጊ ተጫዋቾችን ለማጫወት ሞክራያለው፡፡ የቡድን ስፋት እና ጥራት ላይ ለውጥ አለ፡፡ እነዚህ ልጀች ለሁለተኛው ዙር ለውጥ ያመጣሉ፡፡ በጎዶሎ ተጫዋች ሆነን የአቻነት ግብ በማግኘታችን እጅግ በጣም ተደስቻለው፡፡”
“እግርኳስን ከስህተቱ ነው መቀበል ያለብን፡፡ ብዙ ስህተቶች አይተናል፡፡ ፍፁም ቅጣት ምት ነው አይደለም አትልም፡፡ እግርኳስ በስህተት የተሞላ ነው ይህንን መቀበል መቻል አለብን፡፡”
ጳውሎስ ፀጋዬ – አርባምንጭ
“የዛሬ ጨዋታ እንዳያችሁት ጥሩ እንቅስቃሴ ነው ያረግነው፡፡ ነገር ግን ዳኛው የሰራው ስህተት አሳፋሪ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ዳኝነት በህይወቴም አጋጥሞኝ አያውቅም፡፡ የማያሳጥ ፍፁም ቅጣት ምት ነው የሰጠው፡፡ በመጀመሪያ ዳኛው ሲመደብ እራሱ ብቃት ያለው ዳኛ አይደለም፡፡ ይህ የእኛን ውጤት እና ላብ የገደለ ነው፡፡ እናም በዳኛው በጣም ነው የማፍረው፡፡ ሁሌ ስለዳኝነት እንናገራለን ፤ ግን የሚመደቡ ዳኞችን ተመልከቷቸው፡፡”
“ብዙ ግዜ ግብ ጋር ደርሰናል፡፡ ይህ የነበረብን ክፍተት ነው፡፡ አጨራረሳችን ጥሩ አልነበረም፡፡ ከሌሎች ግዜያት የተሻለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በሂደት እየተሻሻልን ይህንን ለመቅረፍ ጥረት እናደረጋለን፡፡ ተጋጣሚያችን ጥሩ ነው ግን እኛ በልጠን ነው የተጫወትነው፡፡ ሶስት ነጥብ በማጣታችን እጅግ በጣም ከፍቶኛል፡፡”