የ2016 የሲሸልስ ባርክሌይ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ኮት ዲኦር አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል፡፡ ክለቡ የሲሸልስ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩትን ራልፍ ጂያን ሉዊን አዲሱ የክለቡ አሰልጣኝ አድርጎ መቅጠሩ ታውቋል፡፡
በሲሸልስ እግርኳስ ስም ያላቸው ራልፍ የሲሸልስን ብሄራዊ ቡድን በጊዜያዊነት ያሰለጠኑ ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኢትዮጵያ ሲሸልስን ስትገጥም ቡድኑን በአሰልጣኝነት ከመሩ በኋላ ውላቸው በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ በመጠናቀቁ ነበር ከሃላፊነት የተነሱት፡፡ አሰልጣኙ በ2016ቱ የቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣሪያ በቅዱስ ጊዮርጊስ በድምሩ 4-1 የተረታው የሴንት ሚሸል አሰልጣኝም ነበሩ፡፡
ራልፍ ከሲሸልስ የዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር መደልደላቸውን ምክንያታዊ ሲሉ ነበር የገለፁት፡፡ “ቅዱስ ጊዮርጊስ የማውቀው ክለብ ነው፡፡ በብሄራዊ ቡድን ቆይታዬ የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ሲጫወቱ አይቻለው ስለዚህ ይህ ልምዴ ለዝግጅታችን ግብአት ይሆናል” ብለዋል፡፡
ከፈረንጆቹ አዲስ አመት በኃላ ኮት ዲኦር ጠንካራ የስድስት ሳምንት ልምምድ ለማድረግ አቅዷል፡፡ በታሪኩ ለሁለተኛ ግዜ በቻምፒየንስ ሊጉ የሚሳተፈው ክለቡ አዳዲስ ተጫዋቾችንም ለማስፈረም እንደሚመለምልም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኮት ዲኦር በ2015 ካፍ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ደደቢትን ገጥሞ 5-2 መሸነፉ የሚታወስ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስም ከወዲሁ ወደ 1ኛ ዙር የማለፍ ቅድመ ግምቱ በሰፊው ተሰጥቶታል፡፡