ካሜሮን ከ2002 የአፍሪካ ዋንጫ ድል በኃላ የአህጉሪቱን ታላቅ ውድድር ማሸነፍ ተስኗታል፡፡ በ2008 ለፍፃሜ ቢደርሱም የመሃመድ አቡትሪካ የሁለተኛ ግማሽ ግብ ዋንጫው ወደ ግብፅ እንዲያመራ አድርጓል፡፡
የማይበገሩት አንበሶቹ ከ2014 ወዲህ የተጠናከረ ስብስብ ቢኖራቸውም ኮከብ ተጫዋቾቻቸው ብሄራዊ ቡድኑን መቀላቀል አለመፈለጋቸው ብዙ ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡ ስምንት የሚሆኑ የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች የክለብ እግርኳሳቸው ላይ ለማተኮር እንዲረዳቸው የካሜሮንን ጥሪ ችላ ብለዋል፡፡
የአፍሪካ ተሳትፎ ብዛት፡ 17
ውጤት፡ አራት ጊዜ የአፍሪካ ቻምፒዮን (1984፣ 1988፣ 2000 እና 2002)
አሰልጣኝ፡ ሆጎ ብሮስ
ካሜሮን በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ጋቦን፣ ቡርኪናፋሶ እና ጊኒ ቢሳው ጋር ተመድበዋል፡፡ ካሜሮን በማጣሪያው የነበራት የግብ ማስቆጠር ችግር ለቤልጄማዊው አሰልጣኝ ብሮስ ጭንቀት ነው፡፡ በብሮስ ስር የማይበገሩት አንበሶች ካደረጓቸው ሰባት ጨዋታዎች የተሸነፉት በአንድ ብቻ ሲሆን ለአፍሪካ ዋንጫ ካለፉ ሃገራት መካከል ካሜሮን ባስቆጠረቻቸው የግብ መጠኖች የምትበልጠው ቡርኪናፋሶን እና ዩጋንዳን ብቻ ነው፡፡ ብሮስ በወሳኝ ውድድር የሚፈተኑበት ግዜ ቀርቧል፡፡ በ2015 ከምድብ ማለፍ ያልቻለችው ሃገር አሁን ላይ እሩቅ ማለም ትችላለች፡፡
ተስፋ
ካሜሮን በጣም ጠንካራ የሆነ የተከላካይ መስመር አለት፡፡ ግቦችን እምብዛም የማያስተናግደው የተከላካይ መስመሩ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች መገንባቱ ከምድቡ ቢያንስ ለማለፍ በቂዋ ይመስላል፡፡ በምድብ ማጣሪያው ያስተናገደው የግብ መጠን ሁለት ብቻ ነው፡፡ የቪንሶን አቡበከር እና ቤንጃሚን ሙካንጆ ግብ ከማስቆጠራቸው ባሻገር የመሪነት ሃላፊነታቸው መዳበሩ ሌላው የካሜሮን ተስፋ ነው፡፡ የግራ መስመር ተጨዋቹ ኦዮንጎ በጥሩ ብቃት ላይ መገኘት ካሜሮንን ከምድብ ሊያሳልፋት የችላል፡፡ የምትገጥማቸው ሃገራት በዋንጫ ፉክክሩ ላይ የተሰጣቸው ግምት አናሳ መሆኑ ሌላው የካሜሮን ተስፋ ነው፡፡
ስጋት
የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን ራስ ምታት የቡድን ጥልቀቱ መቀነሱ ላይ ነው፡፡ ወደ ስምንት የሚሆነ የቡድኑ ከዋክብት የሃገራቸውን ጥሪ ወደ ጎን በማድረግ ወደ ክለብ ህይወታቸው ፊታችውን አዙረዋል፡፡ እንድ ቹፖሞቲንግ፣ አማዱ እና ማቲፕ ያሉ ተጫዋቾች ማጣት ለብሮስ አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ቡድኑ ጠንካራ ተከላካይ ስፍራ ቢኖረውም የሚያስቆጥራቸው የግብ መጠኖች አነስተኛ ናቸው፡፡ እንደ ሳሙኤል ኤቶ፣ ሮጀር ሚላ እና ፓትሪክ ምቦማ የመሳሰሉ የፊት መስመር ተሰላፊዎችን ያፈራች ሃገር በማጣሪያው በጠባብ ውጤት ተጋጣሚዎቿ ስታሸንፍ ነበር ብዙ ግብ ያስቆጠሩት በመጨረሻው ጨዋታ ጋምቢያ ላይ ነበር(ውጤቱ 2-0 ነው)፡፡ በማጣሪያ ያስቆጠሯቸው የግብ መጠኖች ሰባት ብቻ ነው፡፡ ከምድብ ማጣሪያው የወደቀችው ደቡብ አፍሪካ ከካሜሮን የተሻለ ግቦችን አስቆጥራለች፡፡ ቡድኑ የተስተካከለ የጨዋታ ዕቅድ ለመያዝ ሲቸገር መታየቱም ሌላው ድክመቱ ነው፡፡
የሚጠበቁ ተጫዋቾች
ቤንጃሚን ሙካንጆ በሁለት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ መሻሻልን ያሳየ አጥቂ ሆኗል፡፡ ሙካንጆ ግብ ከማስቆጠር ባለፈ ተከላካዮች መፈተን የመቻል አቅም አለው፡፡ በችግር ግዜያቶች ታማኝነቱን ማሳየቱ የቡድኑ ምክትል አምበል እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ችግሮች በሚታዩበት የፊት መስመር ላይ የሙካንጆ የጨዋታ የማንበብ ብቃት ቡድኑን ይጠቅመዋል፡፡ ሌላኛው የፊት አጥቂው ቪንሰን አቡበከር ነው፡፡ አቡበከር እና ሙካንጆ የተሳካ ጥምረትን ከፈጠሩ ያለጥርጥር ካሜሮን የተሻለ ውጤት ታስመዘግባለች፡፡ አርኖድ ጆም በመሃል ሜዳው ላይ የተለየ እንቅስቃሴ ያሳያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በግራ መስመር የሚጫወተው አምብሮስ ኦዮንጎም ሊታይ ይገባዋል፡፡ የመሃል ተከላካዩ ንኮሎም ሌላው በካሜሮን በኩል ሊታይ የሚገባው ተጫዋች ነው፡፡
የማጣሪያ ጉዞ
በምድብ 13 ከደቡብ አፍሪካ፣ ሞሪታንያ እና ጋምቢያ ጋር የተደለደለችው ካሜሮን ምድቡን በ14 ነጥብ በመጨረስ ወደ አፍሪካው ዋንጫው ያለፈችው፡፡ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ሁለት ግዜ አቻ የተለያየችው ካሜሮን ሞሪታኒያን እና ጋምቢያን በደርሶ መልስ አሸንፋለች፡፡ በተለይ ከሞሪታንያ ከባድ ፈተና ተጋርጦባት በመጨረሻ ደቂቃዎች ባስቆጠረችው ግብ ልታሸንፍ ችላለች፡፡
ሙሉ ስብስብ
ግብ ጠባቂዎች
ጆሴፍ ኦንዶአ (ሲቪያ ቢ/ስፔን)፣ ጆርጀስ ቦክዊ (ኮተን ስፖርት/ካሜሮን)፣ ጁለስ ጎዳ (አጃክሲዮ/ፈረንሳይ)
ተከላካዮች
ኤርነስት ማቦካ (ዚሊኒ/ስሎቫኪያ)፣ ኒኮላስ ንኩሉ (ኦሎምፒክ ሊዮን/ፈረንሳይ)፣ አዶልፍ ቲኩኡ (ሶሾ/ፈረንሳይ)፣ አምብሮስ ኦዮንጎ (ሞንትሪያል ኢምፓክት/ካናዳ)፣ መሃመድ ጂቲ (ታራጎና/ስፔን)፣ ጆሴፍ ንግዌም (ፕሮግረሶ ዶ ሳምቢዛንጋ/አንጎላ)፣ ሚካኤል ንጋዱ (ስላቪያ ፕራግ/ቼክ ሪፐብሊክ)
አማካዮች
ፍራንክ ቦያ (አፔጄስ ደ ሞፎ/ካሜሮን)፣ ጆርጀስ ማንጄክ (ሜትዝ/ፈረንሳይ)፣ ሰባስቲያን ሲያኒ (ኦስተንድ/ቤልጂየም)፣ አርኖድ ጆም (ሃርት ኦፍ ሚድሎቲያን/ስኮትላንድ)፣ ሮበርት ታምቤ (ስፓርታክ ትራናቫ/ስሎቫኪያ)፣ ኮሊንስ ፋይ (ስታንዳርድ ሊየዥ/ቤልጂየም)
አጥቂዎች
ክሊንተን ንጂ (ኦሎምፒክ ማርሴ/ፈረንሳይ)፣ ጃኩዌስ ዞ (ካይዘርስላውተርን/ጀርመን)፣ ቤንጃሚን ሙካንጆ (ሎሪዮ/ፈረንሳይ)፣ ቪንሰን አቡበከር (ቤስኪታሽ/ቱርክ)፣ ኤድጋር ሳሊ (ኑረምበርግ/ጀርመን)፣ ካርል ቶኮ (አንገርስ/ፈረንሳይ)፣ ክሪስቲያን ባሶጎግ (አልቦርግ/ዴንማርክ)
ካሜሮን የምድብ የመክፈቻ ጨዋታዋን ቡርኪናፋሶን ቅዳሜ በመግጠም ትጀምራለች፡፡